ፕሬዚዳንቷን መታደግ ያልቻለችው ቬንዙዌላ እና የትራምፕ ጽኑ ፍላጎት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2018
የፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ታግቶ መወሰድ ተሰማ
ቬንዙዌላዉያን ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት ከእንቅልፋቸው እንደነቁ ፕሬዚዳንታቸው በአሜሪካ ወታደሮች ታግተው መወሰዳቸውን ሲሰሙ ምን ተሰምቷቸው ይኾን? ይህ ቬንዙዌላዉያንን ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምም ዓይን እና ጆሮን ለማመን የሚቸግር ዱብ ዕዳ ነው የሆነው። ቬንዙዌላን የምታክል ሀገርስ እንደምን መሪዋ እንደ አንድ ተራ ነገር ተንጠልጥሎ ሊወሰድባት ቻለ? ያቺ ልዕለ ኃያሏ ሀገርስ ለዓለም ሰላም እና የዴሞክራሲ ጠበቃ ነኝ እንዳላለች ሁሉ ዛሬ መንግሥታት በሕግጋታቸው ቀይ መስመር ብለው ያሰመሩትን የሃገራት ሉዓላዊነት መከበርን እንደምንስ ተላለፈች ? ማዱሮን አሳስሮ ያስወሰዳቸው እንደተባለው የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ሽብር ወይስ እምቅ የሀገሪቱ የነዳጅ ሀብት ክምችት የፈጠረው መጎምዠት? እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ ኃያላን ሃገራትስ የአሜሪካን መንገድ ቢከተሉ የማን ያለህ ይባላል?
ለወራት የዘለቀው የትራምፕ ማዱሮ የቃላት ጦርነት ምናልባትም ሰዓታትን ከወሰደ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ የደቡብ አሜሪካዊቷን ሀገር ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር በማዋል ተጠናቋል። ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ እጃቸው በካቴና ተጠፍንጎ ሲወሰድ የአንድ ሀገር መሪ እና ቀዳማዊት እመቤት ሳይሆኑ በነፍሰ ገዳይነት ተወንጅለው ለዓመታት ሲታደኑ የቆዩ ነበር የሚመስለው።
የወታደራዊ ርምጃው እና የታሪኩ መነሻ
የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ እጅግ ፈጣን ነበር። የካራካስ ከተማ ነዋሪዎች ለቅዳሜ አጥቢያ በውድቅት ሌሊት የዓለምን ፍጻሜ የደረሰ ያስመሰለ ቅጽበታዊ ጥቃቶች እዚህም እዚያም ሲፈጸም አይተዋል አልያም ሰምተዋል። የላ ጉዋይራ ወደብ ፣ የላ ኮርታ አውሮፕላን ማረፊያ እና የሂጉዌሪቲ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የቬንዙዌላ ዋና ዋና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች ናቸው የተባሉ ሁሉ በዚህ ቅጽበታዊ ጥቃቶች ዒላማዎች ነበሩ።
በዚያ ውድቅት ሌሊት በቃጣናው ካሉ ሃገራት አንጻር ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል እንዳላት የሚነገርላት ቬንዙዌላ ፕሬዚዳናቷን ግን መታደግ አልቻለችም። የአሜሪካ የዴልታ ፎርስ (Delta Force) እና የ160ኛው የልዩ ዘመቻ አቪዬሽን ሬጅመንት (SOAR) በቅንጅት ግዳጃቸውን ለዚያውም በደቂቃዎች ውስጥ ተወጥተው ወደ መጡበት ሲመለሱ ተፈላጊውን ሰው ይዘው ነበር።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የነዳጅ ዘይት ማጓጓዣ መርከቦችን በማገት የጀመረው ልዩ ዘመቻቸው በመጨረሻም ያን ለወራት ሲዝቱበት የነበረውን ሰው ካቴና እጁ ውስጥ ሲገባ ፍሎሪዳ ማር አ ላንጎ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሆነው በቀጥታ እየተመለከቱ ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ማዱሮን አሳግተው ከወሰዷቸው በኋላ ተልዕኮው በዚህ እንደማያበቃ አስረግጠው ተናግረዋል። ባለፈው ቅዳሜ ከዋና ዋና የጦር እና የፖለቲካ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው በጋራ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ ቬንዙዌላን የማስተዳደር ፍላጎት እንዳላት ግልጽ አድርገዋል።
«ስለዚህ አስተማማኝ፣ ትክክለኛ እና ፍትኀዊ ሽግግር ማድረግ እስከምንችልበት ጊዜ ድረስ ሀገሪቱን [ቬንዙዌላን] ልንመራ ነው። እና ይህ ደግሞ ፍትኀዊ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ሁላችንም የምንመለከተው ይህንኑ ነው። »
የአሜሪካ ወታደሮች ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በወሰዱ ማግስት ቬንዙዋላዉያን ለሁለት ተከፍለው አደባባይ ወጥተዋል። ገሚሱ የአሜሪካን ውሳኔ ሲደግፍ ገሚሱ ደግሞ ፕሬዚዳንታችንን መልሱልን የሚሉ ድምፆች አሰምተዋል።
ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለአሜሪካው ርምጃ ድጋፍ እና ተቃዉሞ
የአሜሪካን ወንጀል ፈጽማብናለች የሚለው የቬንዙዌላዉያን ድምፅ ግን ጎልቶ ነበር የተሰማው።
«ዩናይትድ ስቴትስ ቬንዙዌላን ለመውረር የወሰደችው እርምጃ ፍጹም ወንጀል ነው። የተቀረው ዓለም አሜሪካ እየፈጸመችብን ያለውን ወንጀል በተመለከተ ግልጽ ምልከታ ሊኖረው ይገባል። ሁሉም በግል ማወቅም አለበት ።»
የቬንዙዌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጌዝን የሀገሪቱ ጊዜያዊ መሪ አድርጎ ሾሟል። ጊዜያዊ መሪዋ ማዱሮ ኅብረተሰባዊት ቬንዙዌላን ለመጠበቅ ላደረጉት ተጋድሎ ከማመስገን አልፈው ፤ አሜሪካ ፕሬዚዳንቱን ወደ ቤታቸው ትመልስ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካ ርምጃ የሚለወጥ ነገር ባይኖርም ከተለያዩ ሃገራት ተቃውሞ ገጥሞታል። የኮሎምቢያው ፕሬዚደንት ጉስቶቭ ፔትሮ መግለጫ ለመስጠት የቀደማቸው የለም። ፕረዚደንቱ አሜሪካ በካራካስ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለቱን ሃገራት ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲያመጣቸው ጥሪ አድርገዋል። ሩስያ በበኩሏ «ድርጊቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የመተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ ነው» ስትል ድምጿን አሰምታለች። ኢራንም ድርጊቱን በይፋ አውግዛለች። ጀርመን ድርጊቱ እንዳሳሰባት ስትገልጽ፤ የአውሮጳ ሕብረትም ዓለም አቀፍ ሕጎች መከበር አለባቸው ብሏል። የኩባው ፕሬዚደንት ሚሄል ዲያዝ በበኩላቸው «በቬንዙዌላ ላይ የተፈጸመ ወታደራዊ ወንጀል» በማለት ነበር ድርጊቱን የገለጹት። ዩናይትድ ኪንግደም በወታደራዊ ዘመቻው እጄ ከደሙ ንጹሕ ነው ብላለች። ለአሜሪካ ድርጊት ብቸኛ ድጋፍ የሰጠችው የቀጣው ሀገር ብራዚል ናት። የብራዚሉ ፕሬዚደንት ጃቬር ሜሊ የቬንዝዌላውን ፕሬዚደንት መያዝ መልካም ዜና በማለት ነበር ደስታቸውን የገለጹት። «በቬንዝዌላ የነጻነት ንፋስ እየነፈሰ ነው፤ ረዥም ዕድሜ ለነጻነት» ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አጋርተዋል።
የታሪኩ መነሻ ወደ ኋላ መለስ ተብሎ ሲቃኝ
አሁን ኒኮላስ ማዱሮ ኒዮርክ ውስጥ በሚገኝ አንዲት ጠባብ እስር ቤት ውስጥ ናቸው። በማንሃተን ፌዴራል ፍርድ ቤት የሕገወጥ የዕጽ ዝውውርን ጨምሮ በርካታ ክሶች ይጠብቋቸዋል። ግን የዚህ ሁሉ መነሻ እና መድረሻ አላማው ምን ይኾን?
ቬኑዙዌላ ከ 300 ቢሊየን በርሜል በላይ የነዳጅ ክምችት በመያዝ ከዓለማችን ተፈጥሮ በለገሰቻት ጸጋ የሚወዳደራት ሀገር የለም ። ይህቺው በተፈጥሮ ሃብቷ የበለጸገችው ሀገር በልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ጥርስ ውስጥ የገባችው ግን በቀድሞው መሪዋ በሁጎ ቻቬዝ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ነው የኋላ ታሪኳ የሚያስታውሰን። ሶሻሊስቱ ቻቬዝ በአውሮጳ ባንኮች ውስጥ ተቀምጦ የነበረው እና በብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የወርቅ ክምችት አስወጥተው መውሰዳቸው ቀዳሚው ጉዳይ ሲሆን ቀጥሎም ቬንዙዌላ ውስጥ የነበሩ የአሜሪካ የነዳጅ አምራች ኩባንያዎችን ከሀገር ማባረራቸው ለአሜሪካዉያኑ ይቅር የሚያስብል አልነበረም።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምሥራቁ ዓለም ርዕዮት አራማጅ ሀገር ከፖለቲካው እንድትገለል እና ኤኮኖሚዋ እንዲንኮታኮት በተለያዩ ማዕቀቦች ተጠፍንጋ እንድትቆይ ተደርጋለች። አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕበመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ያልሞከሩትን ቀን ጠብቀው ምክንያት ፈልገው ፣ አሁን ያደረጉትን አደረጉ።
አሁን ጥያቄው ጉልበተኛዋ ሀገር የአንዲትን ሉዓላዊ ሀገር መሪ ይዛ ስታስር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚወስደው ርምጃ ይኖራል ወይ? ነው ። የዶቼ ቬለው ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው ይህ እንዴት ተደርጎ ይሆናል?
ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሞያው እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኢትዮጵያዊው አቶ ባይሳ ዋቅወያም ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ነው ለዶቼ ቬለ የሰጡት ። ኃያላኑ ከሕግ ተገዢነት እየወጡ ፤ ዓለምን የሚዳኝ ሕግ ዋጋ እያጣ ለመምጣቱም ማሳያ ያዳርጉታል።
የቀዝቃዛው ጦርነት የወለደው እና ዛሬም ድረስ የዘለቀው፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኃያላኑ ሃገራት የርዕዮት ተቃርኖ በቀል በትራቸውን ለማሳረፍ ምክንያት መፍጠራቸው አልቀርም። ዓለም የአንድ ፈረስ ጉግስ ሰለባ ሳትሆን በነበረው የሁለቱ ፈረሶች (አሜሪካ እና ሩስያ) እሽቅድምድም በቅርባቸው ያለ ግን ደግሞ ከጎራቸው ውጪ የዋለውን ሀገር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ለማስገበር የማይፈለነቅሉት ድንጋይ አልነበረም።
የዓለማቀፍ ህግጋት ለአደጋ ተጋልጦ ይኾን?
የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ባይሳ ዋቅወያም የዶናልድ ትራምፕ የቬንዙዌላውን ፕሬዚዳንት አግተው ለመውሰድ የፈጠሩትን ምክንያት ከታሪካዊ ዳራው እያነጻጸሩ ያነሳሉ።
የዶናልድ ትራምፕ ጠንከር ያለው ርምጃ የዓለም አቀፍ ስጋት ከመፍጠር ባሻገር የሚያስቆማቸው ኃይል እንደሌለ በግልጽ እየታየነው። የቬንዙዌላዉያን መጻኢ ዕጣ ፈንታ ግን ገና በውል አልለየም። ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ቬንዙዌላዉያን ለልዕለ ኃያሏ ሀገር እጅ የመስጠቷ እውነታ ሩቅ አይሆንም ።
ይህ በርግጥ አንድ ነገር እንዲሰመርበት ማድረጉ አይቀርም። ኃያላኑ ጥርስ በነከሱባቸው ሃገራት እና መሪዎቻቸው ላይ የበቀል በትራቸውን እንዲያነሱ እና ሃይ ባይ እንዲያጡ ምክንያት ይሆን የሚል። ሩስያ አራተኛ ዓመቷን ባስቆጠረችበት የዩክሬኑ ጦርነት በራሷ መንገድ ተመሳሳይ ርምጃ ብትወስድ የትኛው ሕግ ይዳኛታል? ቻይናስ የግዛቴ አካል ናት በምትላት ታይዋን ላይ ከዚህ የከፋ ርምጃ ብትወስድ በየትኛው ደንብ ማን ሊያስቆማት ይችላል? ጥያቄ በጥያቄ ላይ እየተደራረበ ቢነሳ መልሱ ሩቅ ነው።
መጭው ጊዜ ምን ዋስትና አለው ?
የኾነ ኾኖ ያሉትን ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ የልብ ልብ ያገኙት ዶናልድ ትራምፕ አሁን ፊታቸውን ወዴት ያዞራሉ የሚለውን ጥያቄ በመሠረታዊነት ማንሳቱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም እርሳቸው የጉልበተኛዋ ሀገር አሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸውና።
ባለፈው ሳምንት የኑሮ ውድነት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም የተዳከመባቸው ዞጎቿ ለተቃዉሞ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነችው ኢራን ቀጣይዋ ሀገር ትሆን ?
በጎርጎርሳዊው 1953 በአሜሪካው የስለላ ድርጅት CIA ድጋፍ በኢራኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሞሐመድ ሞሳዴግ ላይ የተፈጸመው የኦፕሬሽን አያክስ ዳግም ዕድል ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታስ አለ?
የጓቲማላው ፕሬዚደንት በ1954 የገጠማቸው ዕድል፣ የቺሊው ፕሬዚደንት ሳልቫዶር አሌንዴ በ1973፣ የዛየሩ ጠቅላይ ሚንስትር ፓትሪክ ሉሙምባ፤ የኢራቁ ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴን በ2003፣ የሊቢያው ፕሬዚደንት ሙአማር ጋዳፊ በ2011 እና ሌሎቹም የውስጥ ተቃዉሞ የሚመስሉ ነገር ግን እንደ ምስጥ ውስጣቸው ገብቶ በሚቦረቡር የአሜሪካ የስለላ መረብ ተተብትበው የወደቁ መሪዎች እና ሃገራት ያተረፉት ነገር ቢኖር ዛሬም ድረስ የዘለቀ የዜጎች የእርስ በርስ ጦርነት እና እልቂት መሆኑ እየታየ ነው። ልዕለ ኃያልነቷን በተግባር እያሳየች ያለችውን ጣልቃ ገቧን ሀገር ግን እረፊ የሚላት ያለ አይመስልም ። ወይም አይኖርም።
ታምራት ዲንሳ