1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ከባድ ጥቃት በመፈጸም የሐገሪቱን ፕሬዚደንት መያዝዋን አስታወቀች።

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 25 2018

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ፕረዚደንቱ በአሜሪካ ልዩ ሐይሎች መያዛቸውን አረጋግጠው ለፈጸሙት ወንጀል «በሕግ ይጠየቃሉ »ብለዋል። የቬንዙዌላ መንግስት በበኩሉ ስለሐገሪቱ ፕሬዚደንት መያዝ እስከአሁን ያለው ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/56GW7
Venezuela Caracas 2026 | Rauch über Caracas nach nächtlichen Explosionen in der Stadt
ምስል፦ REUTERS

ዩናይትድ ስቴትስ በቬንዙዌላ ላይ ከባድ ጥቃት በመፈጸም የሐገሪቱን ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ መያዝዋን አስታወቀች። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ «ትሩዝ ሶሻል» በተባለው የግል ማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ሐገራቸው በቬንዙዌላ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸሟንና የሐገሪቱን መሪ መያዛቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ፕረዚደንቱ በአሜሪካ ልዩ ሐይሎች መያዛቸውን አረጋግጠው ለፈጸሙት ወንጀል «በሕግ ይጠየቃሉ »ብለዋል።
የቬንዙዌላ መንግስት በበኩሉ ዩናይትድ ስቴትስ በስቪልና ወታደራዊ ተቋሞቼ ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች ከማለት ውጭ ስለሐገሪቱ ፕሬዚደንት መያዝ እስከአሁን ያለው ነገር የለም። በዋና ከተማዋ ካራካስ 7 ከባባድ ፍንዳታዎች እንደተሰሙ የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። ሔሊኮብተሮችና ወታደራዊ አውሮፕላኖች በካራካስ ሰማይ ሲያንዣብቡ መታየታቸውን የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ገልጸዋል።
የቪንዝዌላ መንግስት  ባሰራጨው መግለጫ ዩናይትድስቴትስ የፈጸመችውን ጥቃት «በጣም ከባድ ወታደራዊ ወረራና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን የጣሰ ድርጊት» ብሎታል። NTN24 የተባለውን የሐገሪቱ ቴሌቪዝን ያሰራጨውን የተንቀሳቃሽ ምስልን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው። በከተማዋ ከባባድ ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ ከፍተኛ ጭስ  መታየቱን አመልክቷል። ስለደረሰው ጉዳት እስከ አሁን የተባለ ነገር የለም።
የኮሎምቢያው ፕሬዚደንት ጉስቶቭ ፔትሮ አሜሪካ በካራካስ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱን ሐገራት ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲያመጣቸው ጥሪ አድርገዋል። ሩስያ በበኩሏ ድርጊቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ ስትል  ተቃውማለች።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን ለሮይተርስ በሰጡት አጭር ምላሽ ሐገራቸው ጥቃቱን መፈጸሟን አምነው ዝርዝር ጉዳይ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኞ በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተው እንደነበር ይታወሳል። ፕሬዚደንት ማዱሮ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው በማመልከት።

የአሜሪካ አሁናዊ የጥቃት መነሻ


የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ በቬንዙዌላ ላይ ጥርሱን የነከሰው ወደ አሜሪካ የሚገቡ የአደንዛዥ ዕጾች መነሻ ናቸው ብለው ከዘረዘሩዋቸው ሐገሮች ተርታ ቬንዙዌላ ከፊት ረድፍ በማሰለፉ ነው። ለአሜሪካ ጤናና ደሕንነት ስጋት ነው ያለውን  የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር በፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ በምትመራው  ቬንዙዌላ አማካኝነት ወደ አሜሪካ እንደሚገባ በመግለፅ የትራምፕ አስተዳደር  በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎች አነስተኛ ጀልባዎች ጥቃት ፈጽሟል። እ.አ.አ .አቆጣጠር ከሕዳር ወር 2025 መጨረሻ ወዲህ አሜሪካ «የዕጽ አዘዋዋሪዎች ናቸው» ያለቻቸውን 115 ሰዎች በአየር ጥቃት መግደሏን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የቬንዙዌላ ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ
የቬንዙዌላ ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮምስል፦ Federico Parra/AFP

የርዕዮተ ዓለም ልዮነት


አሜሪካ ለአሁኑ ጥቃቷ የአደገኛ ዕጽ ዝውውርን እንደሽፋን ብትጠቀምበትም የፖለቲካ ተንታኞች ግን ሁለቱም ሐገራት ያላቸውን የርዕዮተዓለም ልዩነት አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲፈራረጁ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ። አሜሪካ «የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትከተል ስትሆን ቬንዝዌላ ደግሞ በተለይ እ.አ.አ በ1990 ዎቹ መጀመሪያ ሁጎ ቻቬዝ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ግራ ዘመም የሕብረተሰባዊነት ርዕዮት ትከተላለች። ሑጎ ቻቬዝ ደግሞ አሜሪካ የነጻ ገበያ ሥርዓቷን ወደ ላቲን አሜሪካ ሐገሮች እንዳታስፋፋ እራሳቸው እንደ ተከላካይ አጥር አድርገው ይመለከቱ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሑጎ ቻቬዝ እ.አ.አ በሚያዝያ ያ 5 ቀን 2013 መሞታቸውን ተከትሎ በመጋቢት 14 ቀን  2014 በተካሄደ አስቸኳይ ፕረዚደንታዊ ምርጫ የሐገሪቱ ፕረዚደንት ሆነው የተመረጡትና አሁን ሐገሪቱን እያስተዳደሩ የሚገኙት ኒኮላስ ማዱሮም በራቸውን ለነጻ ገባያ ክፍት ባለማድረጋቸው ቁርሾው ሳይበርድ በጠላትነት የመፈላለጉ ጉዳይ እንደቀጠለ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአሜሪካ ኩባንያዎች መወረስ


ቬንዝዌላ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ካላቸው ሐገሮች ተርታ የምትመደብ ሐገር ናት። እ.አ.አ በ1990 ዎቹ መጀመሪያ የስልጣን እርካብ የተቆናጠጡት ሑጎ ቻቬዝ በሐገሪቱ የነበሩትን የአሜሪካ ነዳጅ አምራች ኩባንያዎችን ወርሰዋል። ይህ ከሕብረተሰብአዊነት መርሕ አንጻር የወሰዱት የመውረስ እርምጃ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ለምትመራው አሜሪካ ትልቅ ራስ ምታት ነበር የሆነባት። በሐገሪቱ የተጀመረውን የሕብረትሰብአዊነት ስረዓት እንዳይስፋፋ የምትጥረው አሜሪካ ይባስ ብሎ በሑጎ ቻቬዝ መንግስት ኩባንያዎቿ መወረሳቸው ጸቡ እንዲካረር ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሊሉ።

ጂኦፖለቲካዊ ምክንያት

የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕረጢደንት ከቀድሞው የኢራን ፕረዚደንት መሐመድ ኻታሚን
የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕረጢደንት ከቀድሞው የኢራን ፕረዚደንት መሐመድ ኻታሚንምስል፦ UPI/IMAGO


አሜሪካና ቬንዜዌላ በባላንጣነት እንዲተያዩ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ሌላኛው የአካባቢው ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው። ቪንዙዌላ የአሜሪካ ተቀናቃኝ ከሚባሉት እንደነ ሩስያ፣ ቻይና፣ ኩባ እና ኢራን የጠበቀ ግኑኝነትን ፈጥራለች። ይህ ጠንካራ ግንኙነት የነጻ ገበያ መርሕ እከተላለለሁ ለምትለው አሜሪካ እረፍት የሚሰጥ አልነበረም። በመሆኑም አሜሪካ የነዳጅ ምርቶች ገበያን ጨምሮ በቬንዙዌላ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ማድረጓ ዘገባዎች ያመላክታሉ።


ከዚህስ በኋላ ምን ይከተል ይኾን?


የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሰኞ በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተው  ፕሬዚደንት ማዱሮ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው አስጠንቅቀው ነበረ። ዛሬ እንደተሰማው ፕሬዚደንት ማዱሮ እና እና ባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ከሀገር መውጣታቸው ተሰምቷል። ምንም እንኳ የቬንዙዌሎላ መንግስት ማረጋገቻ ባይሰጥበትም። የፕሬዚደንቱ ተነጥለው መያዝን ተከትሎ አሜሪካ እንደምትሻው በቬንዝዌላ የርዕዮተ አለምና የመንግስታዊ ለውጥ ይመጣ ይኾን? 

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ታምራት ዲንሳ