የቬንዙዌላው ፕሬዚደንት ኒኮላስ ማዱሮ የዕጽ ዝውውር የሽብር ወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ነው
እሑድ፣ ታኅሣሥ 26 2018
በአሜሪካ ወታደሮች ከባለቤታቸው ጋር ታስረው ወደ ኒዮርክ የተወሰዱት ማዱሮ በማንሃተን ፌዴራል ፍርድ ቤት የህገወጥ የዕጽ ዝውውርን ጨምሮ በርካታ ክሶች ይጠብቋቸዋል ነው የተባለው።
የማዱሮን መወሰድ ተከትሎ የቬንዙዌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንቷን ዴልሲ ሮድሪጌዝን የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት አድርጎ ሾሟል። ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቷ ማዱሮ ህብረተሰባዊት ቬንዙዌላን ለመጠበቅ ላደረጉት ተጋድሎ ከማመስገን አልፈው ፤ አሜሪካ ፕሬዚዳንቱን ወደ ቤታቸው ትመልስ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ቻይና እና ሩስያን ጨምሮ ጥቂት የደቡብ አሜሪካ ሀገራት የአሜሪካን ርምጃ መቃወማቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ዛሬ ባወጡት መግለጫ የቬንዙዌላ አስተዳደር ከአሜሪካ ጋር መተባበር ከቻሉ አብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ሩቢዮ CBS ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ቬንዙዌላዉያን መሪዎች "ሁሉንም ነገር በሚያደርጉት ነገር ልክ እንመዝናቸዋለን " ብለዋል።
ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን አሜሪካ በድጋሚ« የምትሰዳቸውን ርምጃዎች ለማጤን» ትገደዳለች ብለዋል።
የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ስር ሲውሉ በቀጥታ ስርጭት ይከታተሉ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ «የቴሌቪዥን ፕሮግራም እየተመለከትኩ እንዳለሁ ነበር የተሰማኝ» ሲሉ ራሳቸው ያዘዙትን ወታደራዊ ዘመቻ አስመልክቶ ተናግረዋል። አክለውም ትራምፕ «አሜሪካ ማድረግ የምትችለውን በዓለም ላይ ማድረግ የሚችል ሀገር የለምም» ሲሉ ትራምፕ በጉራ ተናግረዋል።