"ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ምሥረታ
"ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በምሥረታ ላይ መሆኑን የሀሳቡ ጠንሳሽ እና ሂደቱን የሚያስተባብሩት ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ ዛሬ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። አዲሱ "ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" እየተቋቋመ ያለው በሁለት የኦፌኮ የቀድሞ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በሥራ አሥፈጻሚ ውስጥ የነበሩ ሰዎች እና ሌሎችም ነው ተብሏል። ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ"የሕዝብ እና የሀገር ጥያቄ ሳይስተካከል በመቅረቱ ይህንን ፓርቲ እያቋቋምን እንገኛለን " ብለዋል፤
በመመስረት ላይ የሚገኘው ይኼው "ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ መሳተፍ አልሞ እንደነበር የነገሩን አቶ ደስታ አሁን ባለንበት ኹኔታ ግን በቀጣዩ ምርጫ ስለመሳተፋችን "እርግጠኛ አይደለሁም" ብለዋል። የፓርቲ ምሥረታ ሥራው ከአንድ ዓመት በፊት መጀመሩን የገለፁት አስተባባሪው የ10 ሺህ አባላት ስብሰባ ተጠናቋል፣ መተዳደርያ ደንብ፣ አርማ፣ ስያሜ እና የመመስረቻ ጽሑፍም ተዘጋጅቷል" ብለዋል።
ኢራን፤ መንግሥት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ማብረዱን አስታወቀ
በኢራን በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ መንግሥት ማብረዱን አስታወቀ። በመንግስት የሚተዳደረው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ኢራብኒውስ እንደዘገበው አብዛኞቹ የሀገሪቱ ከተሞች በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ይገናሉ። አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች "የታጠቁ አሸባሪዎች" ያላቸው ተቃዋሚዎች የህዝብን ደህንነት ለማደፍረስ ሞክረዋል። እንደዛም ሆኖ በጸጥታ ኃይሎች እና በህዝቡ ድጋፍ ኃይል የተቀላቀለበት ግጭት ውስጥ ሳይገባ ቀርቷል። ሲል ዘግቧል።
የኢራን መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎትን እና የስልክ መስመሮችን በመዝጋቱ የተነሳ መረጃ የማግኘት ውስንነት አለ። የኢንተርኔት እና የስልክ መስመሮች ከመዘጋታቸው በፊት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተጋሩ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት እንደ ቴህራን እና ማሻድ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ሰዎች መንግሥትን ለመቃወም አደባባይ ወጥተው ነበር።
ኢራን ውስጥ ለ13 ቀናት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በትንሹ 65 ሰዎች መሞታቸውን የመብት አቀንቃኞች ተናግረዋል። ከ2,300 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
ሶሪያ፤ የሶሪያ ጦር አሌፖን መቆጣጠሩን አስታወቀ
ለቀናት ከዘለቀ ውጊያ በኋላ የሶሪያ ጦር አሌፖ ከተማን ከኩርድ ተዋጊዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረጉን ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት አስታወቀ። የኩርድ ተወካዮች የሶርያ ጦርን መግለጫ አጣጥለው ውጊያው ቀጥሏል ብለዋል።
የሶሪያ መንግስት ሃይሎች እና የኩርድ ተዋጊዎች ከማክሰኞ አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በሚኖርባት የሶሪያዋ ጥንታዊ ከተማ አሌፖ ላይ እየተፋለሙ ይገኛሉ። እንደ አዣንስ ፍራንስ ዘገባ በውጊያው ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የጊዜያዊው ፕሬዝደንት አህመድ አል ሻራ ወታደሮች በኩርድ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የሼክ ማክሱድን አካባቢ 55 በመቶ ክፍል መቆጣጠራቸውን የአልጀዚራ አረብኛ ዝግጅት ቀደም ብሎ የሶሪያ ጦርን ዋቢ አድርጎ መዘገቡን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል።እንደ ዜና አውታሩ መረጃ በአካባቢው የተካሄደውን ውጊያ ሸሽተው የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር 162,000 ደርሷል።
ለቀናት በአሌፖ የዘለቀው ውጊያ ከአንድ አመት ገደማ በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ከባዱ ነው ተብሏል። በከተማዋ ለአርብ አጥቢያ ለተወሰኑ ሰዓታት የተኩስ አቁም ተግባራዊ ሆኖ ነበር። እንደ መንግስት ገለጻ ይህ የሆነው የኩርድ ተዋጊዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚኖርባትን ከተማ አሌፖ በፈቃደኝነት ለቀው እንዲወጡ እድል ለመስጠት ነው። ይሁንና የኩርድ ተወካዮች ለመልቀቅ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ይበልጡ ክፍል አሁንም በኩርድ መከላከያ ኃይል በምዕፃሩ SDF ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር ይገኛል።
በዚህ በክረምት ወቅት ይበልጥ መባባሱን የጀርመን ቀይ መስቀል ድርጅት አስታወቀ
ቀድሞውኑም ችግር ላይ ያሉት የጋዛ ሰርጥ ነዋሪዎች ሁኔታ በዚህ በክረምት ወቅት ይበልጥ መባባሱን የጀርመን ቀይ መስቀል ድርጅት አስታወቀ። "ደካማ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ተጨምሮበት የክረምት ወራቱ በተለይ ለህጻናት፣ ለተጎጂዎች እና ለአረጋውያን ከባድ ሆኗል" ሲሉ የጀርመን ቀይ መስቀል ድርጅት ፕሬዝዳንት ሄርማን ግሮኸ ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ መግለፃቸውን የጀርመን ዜና ምንጭ ዲፒኤ ዘግቧል። "አሁንም ምግብ፣ የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት፣ መብራት እና ውሃ እጥረት አለ" ሲሉም የቀድሞው የጀርመን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ግሮኸ አሳስበዋል። ግሮኸ እንዳሉት ከተቁስ አቁሙ በኋላ የሰብዓዊ ርዳታ ሁኔታው በጋዛ ሰርጥ ቢሻሻልም፤ በየዕለቱ የሚያስፈልጉት 600 የጭነት መኪና ሰብዓዊ ርዳታዎች እስካሁን ሊሟሉ አልቻሉም።
እንደ ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ገለፃ በጋዛ ሰርጥ የህክምና አገልግሎት እጦት ትልቅ ችግር ፈጥሯል። የቡድኑ ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን ካትሰር “ብዙ ፍልስጤማውያን ሊታከሙ በሚችሉ በሽታዎች እየሞቱ ነው” ሲሉ ለጀርመኑ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ቢያንስ 439 ፍልስጤማውያንን ገድለዋል ሲል በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትናንት አስታውቋል።ሆኖም የሟቾቹ ቁጥር በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጥም።
በዩክሬን በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ በሩሲያ አንድ ነዳጅ ማከማቻ ተቃጠለ
ሩሲያ እና ዩክሬን ሌሊቱን አንዳቸው ሌላቸው ላይ በሰነዘሯቸው የድሮን ጥቃቶች በሰው እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ። በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን የዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል አስተዳዳሪ ኦሌክሳንደር ሃንሻ እንዳሉት በክልሉ ዋና ከተማ ዲኒፕሮ ሶስት ሰዎች ቆስለዋል።በከተማዋ በሚገኝ የኃይል አገልግሎት አቅራቢ ላይ በደረሰ ጉዳትም የኤሌክትሪክ አቅርቦት መቋረጡ ተዘግቧል። የክልሉ አስተዳዳሪ ሃንሻ 27 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማክሸፍ መቻሉንም ተናግረዋል።
በሩሲያ በኩል በዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አንድ የነዳጅ ማከማቻ የእሳት ቃጠሎ ደርሶበታል። የሩሲያ ቮልጎግራድ ክልል አስተዳዳሪ ስለ ጉዳቱ መጠን ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ የአካባቢው ነዋሪዎችን በቃጠሎው ምክንያት ከስፍራው እንዲሸሹ መደረጉን ዛሬ ቅዳሜ ተናግረዋል። ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ሰሞኑን የሰነዘረችውን ከፍተኛ ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።ሩሲያ መካከለኛ ርቀት ያለው ሚሳኤሏን ዩክሬን ላይ ዳግም ትናንት ተኩሳለች። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ይህ ለመላው አውሮፓ ስጋት እንደሆነ አሳስበዋል።
የጂ7 ጉባኤ ለትራምፕ ልደት ሲባል አንድ ቀን ተገፋ
የጂ7 ጉባኤ ለትራምፕ ልደት ሲባል አንድ ቀን ተገፋ። የበለፀጉ ሀገራት የሚሳተፉበት የጂ7 ጉባኤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከሰኔ 14-16 እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም በዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ80ኛ የልደት በዓል ምክንያት ከታቀደለት ቀን እንዲገፋ መደረጉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። የትራምፕ የልደት በዓል ሰኔ 14 ቀን በዋይት ሀውስ ይካሄዳል።
የዘንድሮው የG7 ጉባኤ በፈረንሳይ የሚካሄድ ሲሆን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደዘገበው ጉባኤው ከሰኔ 15-17 እንዲዛወር ተደርጓል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ጉባኤው ወደ ሌላ ቀን የተገፋው "ከጂ7 አጋሮች ጋር በተደረገው ምክክር" መሆኑን ተናግረዋል። የጂ7 አመታዊ ጉባኤ በአባል ሀገራቱ በዙር ይካሄዳል።
ዩናይትድ ስቴትስ በትራምፕ የልደት ቀን ማለትም ሰኔ 14 ቀን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ታከብራለች። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ2022 በስልጣን ላይ እያሉ 80 ዓመት የሞላቸው ቢሆንም፣ በአነስተኛ ዝግጅት ማክበርን መርጠው ነበር ሲል ዘገባው አመልክቷል።