1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የእስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠት የተፈጠረው ውዝግብ ወዴት?

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2018

ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት በላይ የዘለቀው ጥበቃ አሁን ባልተጠበቀ ሁኔታ ተስፋ የፈነጠቀላት መስሏል። እስራኤል ለሶማሌ ላንድ የሉአላዊ ሀገርነት እውቅና ስትሰጥ የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገር ሆናለች።

https://p.dw.com/p/565kC
የእስራኤል ለሶማሊላንድ የእውቅና መስጠት የተፈጠረው ውዝግብ ወዴት?
የእስራኤል ለሶማሊላንድ የእውቅና መስጠት የተፈጠረው ውዝግብ ወዴት?ምስል፦ Farhan Aleli/AFP/Getty Images

የእስራኤል ዕውቅና መስጠት ይቀለበስ ወይስ ሌላ ተከታይ ያፈራ ይኾን?

ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት በላይ የዘለቀው ጥበቃ አሁን ባልተጠበቀ ሁኔታ ተስፋ የፈነጠቀላት መስሏል። እስራኤል ለሶማሌ ላንድ የሉአላዊ ሀገርነት እውቅና ስትሰጥ የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገር ሆናለች። ይህ በርግጥ ለሶማሊያ ዱብ ዕዳ ፣ ለኢትዮጵያ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ዝምታን፤  ከኢራን እስከ ቱርክ፣ ከግብጽ እስከ ቃጣር ተቃውሞና የዲፕሎማሲ ሩጫ ፣ የአፍሪቃ ህብረት እና የመንግስታቱ ድርጅትን ውግዘት፣ የልዕለ ኃያሏን ሀገር አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ  የለበጣ ተቃዉሞ ቢያስከትልም ፤ የሶማሌ ላንድ ነዋሪዎችን ለደስታ አደባባይ ከመውጣት አላገዳቸውም ። ሀገር እንደ ሀገር ሲቀበላቸው ይህ የመጀመሪያቸው ነውና !
የታሪኩ ጅማሬ ወደ ወርሃ ግንቦት 1983 ዓ.ም ይወስደናል። ኢህአዴግ ከሁሉም አቅጣጫ የአዲስ አበባ ከተማን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ከበባ ማድረግ የጀመረበት ሰሞን ። የወቅቱ የኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ከአዲስ አበባ ወደ ሃራሬ፤ ዚምባብዌ ለመኮብለል በቻርተር አውሮፕላናቸው የተነሱበት ዕለት ፤ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ነበር። ኢትዮጵያዉያን ራሳቸውን ከርስ በርስ ጦርነቱ ነበልባል ለማትረፍ የሚሯሯጡበት ወቅት ነውና የሀገራቸውን መጻዒ ዕጣ ፈንታን ገና በውሉ አልለዩም።  
ከሰሜን ኢትዮጵያ ተነስቶ መላው ሀገሪቱን አካሎ መዲናዪቱ ላይ ሊቋጭ ከጫፍ የደረሰው ጦርነት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ ፍላጎት የሚያሳድር አይመስልም። ነገር ግን የሰሜናዊ ሶማሊያ አንዲት ግዛት ራሴን ችዬ ሀገር ሆኛለው ስትል ለተቀረው ዓለም ራሷን ገልጣለች። የአፍሪቃ ቀንድ ትኩሳት በተለይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በብሔር እና ጎሳ ተከፋፍለው ለከፋ የርስ በርስ ጦርነት እና ዕልቂት እንዳይዳረጉ ወቅቱ አስፈርቷል።
 ይህ ብቻም አይደለም ፤ የርስ በርስ ጦርነቶቹ ያስከተሏቸው መዘዞች ሃገራቱ  የግዛት አንድነታቸው ተንዶ ሊበታተኑ  ከሚችሉበት ጫፍ ላይ መድረሱ ከባህረ ሰላጤው የኢራቁ የሳዳም ሁሴን እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትልቁ ጆርጅ ቡሽ ያስተባበሩት ጥምር ኃይል ከገጠሙት ጦርነት የተረፈውን የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ስቧል። 

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ውል ባሰረችበት ወቅት
ኢትዮጵያ ከግዛቴ ጋር ውል አሰረች ብለው እንዳደረጉት ከአስመራ ፣ ካይሮ ፣ ከካይሮ አንካራም አልበረሩምምስል፦ TIKSA NEGERI/REUTERS


በብዙ የተፈራው አልቀረም።  ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ በይፋ ራሴን ችያለሁ ባለችበት ዋዜማ ሶማሌ ላንድም ከሶማሊያ ተገንጥላ ሀገር መሆኗን አወጀች ። ግንቦት 13 ቀን፣ 1983 ዓ.ም ።  ይህ ቀን  ለኢትዮጵያም ሆነ ሶማሊያ በርግጥ የጨለማ ቀናቸው ነበር ። ኢትዮጵያ የባህር በሯን ወዳም ይሁን ተገዳ አሳልፋ የሰጠችበት ፤ ሶማሊያም ተገንጣይዋን ግዛት ለማቆም አቅም ያጣችበት ። 
የጉዳዩን ዓለማቀፋዊ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እና ምላሽ እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት ሕግጋት እንደምን የኤርትራን መገንጠል ተቀብሎ እንደምንስ የሶማሌ ላንድን እስከ ዛሬም ድረስ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ? ኋላ እንመለስበታለን ። አሁን የእስራኤል ለሶማሌ ላንድ የሰጠችው ዕውቅና እና የአለማቀፉን ማህበረሰብ ምላሽ ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት ።

«ክቡር ፕረዚዳንት ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ፣ ከርስዎ ጋር በመነጋገሬ ደስ ብሎኛል።  ከምንም ነገር በፊት ግን ፣ አሁን ከእርስዎ ጋር በምንናገርበት ቅጽበት  እስራኤል ለሶማሊ ላንድ በይፋ እውቅና መስጠቷን  እና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቷን የምታከብር መሆኑን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ። ለዚህ ደግሞ  በጣም ደስተኛ ነኝ።  እናም ለዚህ ቀን በጣም ኩራት የሰማኛል።  ለሶማሌ ላንድ ሕዝቦችም መልካሙን  ነገር ሁሉ እመኛለሁ። »

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ
እስራኤል ለሶማሊ ላንድ በይፋ እውቅና መስጠቷን  እና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብቷን የምታከብር መሆኑን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁምስል፦ Abir Sultan/AP Photo/picture alliance

እስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ከሶማሌ ላንድ ግዛት ፕሬዚዳንት አብዲራህማን መሐመድ አቡዱላሂ ጋር ባለፈው ዓርብ በስልክ ባደረጉት ንግግር ነበር እስራኤል ለሶማሊላንድ በይፋ የሀገርነት ዕውቅና መስጠቷን ያስታወቁት። ይህ ለ34 ዓመታት ሀገር ሆና እንደሀገር መቆጠር ለተሳናት ግዛት ከአንድ የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገር እውቅና ማግኘት ምን ማለት እንደሆነ በዕለቱ በርበራ ከተማ ውስጥ ደስታውን ለመግለጽ አደባባይ የወጣውን የከተማዋን ነዋሪ መመልከት ብቻውን በቂ ነው። 
ሃገራት ለተንገጣይ ግዛቶች በተናጥል ዕውቅና መስጠት የነበረ የሃገራቱ ሉዓላዊ መብት ቢሆንም የእስራኤል በባብኤል መንደብ መገኘት እና ትናንት ጎረቤት የነበረችው ኢትዮጵያ እውቅና ለመስጠት በመሞከሯ ብቻ የተፈጠረባትን ትርምስ ላስታወሰ ዐይኑን ከፍቶ፣ ጆሮውን አስፈቶ ጉዳዩን በአንክሮ መመልከቱ አይቀርም። የዶቼ ቬለው ነጋሽ መሐመድ እንደሚለው የእስራኤል ሶማሊ ላንድ መገኘት በርግጥ አዲስ ነገር ይዞ መምጣቱ አይቀርም። 

እስራኤል ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ከሶማሊያ በፊት የተቃዉሞ ድምፃቸውን ያሰሙት ግብጽ ፣ ጂቡቲ እና ቱርክ ነበሩ ።የአፍሪቃ ህብረት ፣ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ የአውሮጳ ህብረት ፣ በተከታታይ የመንግስታቱን ድርጅት የግዛት አንድነት ይከበር መርህ እየጠቀሱ የእስራኤልን ዕውቅና መስጠት በየራሳቸው ቋንቋ ተቹ ፣ ተቃወሙ፣ አልያም አወገዙ። ዋናዋ ሶማሊያ ለእስራኤል ድርጊት ወዲያው ምላሽ አልሰጠችም ።

ፕሬዚዳንቱ  ሀሰን ሼክ መሐመድ ልክ ኢትዮጵያ ከግዛቴ ጋር ውል አሰረች ብለው እንዳደረጉት ከአስመራ ፣ ካይሮ ፣ ከካይሮ አንካራም አልበረሩም። ምክንያቱም ሀገሪቱ እስራኤል ናትና ። ነገር ግን ጊዜ ገዝተው ትናንት እሁድ ምክር ቤታቸውን በአስቸኳይ ሰብስበው በእስራኤል ላይ ውግዘት ማሰማታቸው አልቀረም። ፓርላማው በሉአላዊነቴ ላይ «ሆን ተብሎ የተቃጣ ጥቃት» ሲል ድርጊቱን በይፋ ፈርጆታል። የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት አቶ አብዱራህማን ሰይድ የእስራኤል ርምጃ በቀጣናው ከሩቅም ከቅርብም ሃገራትን የሚጋብዝ ትርምስ የመፍጠር ዕድል እንዳለው ነው የሚናገሩት ።
«ቀጣናውን እንደገና የጦርነትና የታላላቅ ሃገራት መተራመሻ አካባቢ ሊሆን ነው ማለት ነው። ምክንያቱን እንደሚታየኝ ሶማሌ ላንድ በቀጥታ ከእስራኤል ጋር መስራት ሊጀምሩ ነው። እዛም የጦር ሰፈርም ሌላም ሊሰጡ ይችላሉ ። ኢትዮጵያኖቹ ከእስራኤል ጋር ሊሰለፉ ይችላሉ ፤ ሌሎቹም የደቡብ ሱዳንም ፣  ህንድም ሌሎችም እዚህ ላይ ሊገቡ ይችላሉ ።…ፍጥጫው ሊቀጥል ይችላል።»

የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ
የእስራኤል ርምጃ በቀጣናው ከሩቅም ከቅርብም ሃገራትን የሚጋብዝ ትርምስ የመፍጠር ዕድል እንዳለው ነው የሚነገው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በዚሁ የእስራኤል ሶማሌ ላንድ ጉዳይ ኒው ዮርክ አሜሪካ  ውስጥ ሊመክር ለዛሬ ሰኞ ቀጠሮ ይዟል። ምክር ቤቱ ዶሃ ቃጣር ውስጥ በተመከረ እና  አብዛኞቹ ሙስሊም ከሆኑ 21 ሃገራት የቃዉሞ ጥሪ ከተላለፈ በኋላ የተጠራ ነው ተብሏል። 


የእስራኤል ርምጃ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዘንድ የተለያየ ስሜት የፈጠረ መስሏል። ኤርትራ በይፋ ባወጣችው መግለጫ ተቃውሞዋን ስትገልጽ ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት «የማያሻማ» መልስ እንዲሰጥ ጠይቃለች።  የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ግን ስለጉዳዩ ዝምታን የመረጡ መስለዋል። እንዲያውም ዋነኞቹ የመገናኛ ብዙኃን ዓለም የተቀባበለውን ጉዳይ ወዲያው አልዘገቡም።  
የቀጣናውን ጉዳይ የሚከታተሉት አቶ አብዱራህማን ሰይድ እንደሚሉት ግን የእስራኤል ርምጃ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር ይዞ ሳይመጣ እንዳልቀረ ነው ። 

ሶማሊላንዳዉኢን በአደባባባይ ደስታቸውን እየገለጹ
የአፍሪቃ ህብረት እና የመንግስታቱ ድርጅትን ውግዘት፣ የልዕለ ኃያሏን ሀገር አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ  የለበጣ ተቃዉሞ ቢያስከትልም ፤ የሶማሌ ላንድ ነዋሪዎችን ለደስታ አደባባይ ከመውጣት አላገዳቸውም ።ምስል፦ Farhan Aleli/AFP/Getty Images


«ለኢትዮጵያ አንደኛ ጥሩ ዜና ነው። ምክኒያቱም በ2024 ጥር አካባቢ ስምምነት ሲፈራረሙ በዚያን ጊዜ ለነበረው የሃርጌሳው መሪ ዕውቅና ለመስጠት ነበር ። ነገር ግን አልደፈሩትም።  ምክንያቱም ከአፍሪቃ ቻርተርና ከብዙ ሌላ ጉዳዮች የሚጋጭ ስለሆነ ሊደፍሩት አልሞከሩም….አሁን ግን እስራኤል በይፋ አድርጋዋለች ስለዚህ ኢትዮጵያኖች በጣም ደስታ ነው ለመንግስት ።»
ሶማሊላንድ የአሁኑ ስያሜዋን ለማግኘቷ አውሮጳዉያኑ ቅኝ ገዢዎቿ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በጎርጎርሳዉያኑ 1880 የአሁኑን የሶማሊላንድ ግዛት በወረራ ይዛ የነበረው እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሪቲሽ ሶማሊላንድ ብላ ሰየመችው ። ከቦሳሶ ከተማ ጀምሮ እስከ ታችኛው የሶማሊያ ክፍል በወረራ የያዘችው ሌላዋ አውሮጳዊት ሀገር ጣልያን በበኩሏ ጣልያን ሶማሊላንድ ስትል ሰይማለች። ሶማሊያ ወደ አንድነቷ ከመምጣቷ አስቀድመው ግዛቶቹን የሁለት ሀገርነት ስነ ልቦና አላበሷቸው ። ይህም ግዛቶቹ በጎርጎሪዮሱ 1960 ነጻነታቸው እስኪጎናጸፉ ድረስ የቆየ ነበር። አንድ እምነት እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው ሕዝብ በጎሳ እና በተከፋፈለ ስነ ልቦና ውስጥ ቢቆይም የኋላ ኋላ የአንድነት መንግስት መመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከመፈጸም ግን አላገዳቸውም ።

ሶማሊያ
አንድ እምነት እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው ሕዝብ በጎሳ እና በተከፋፈለ ስነ ልቦና ውስጥ ቢቆይም የኋላ ኋላ የአንድነት መንግስት መመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከመፈጸም ግን አላገዳቸውም ።ምስል፦ DW

ሞቃዲሾን ዋና ከተማው አድርጎ የተመሰረተው የሶማሊያ መንግስት የጸና መሰለ። ይህ ግን ብዙ መጓዝ አልቻለም። የስልጣን ክፍፍሉ የግዛቶቹን የአንድነት ምስረታ ውል ለመናድ ጊዜ አልወሰደበትም ። ሶማሌላንዳዉያን በመንግስት ምስረታ ውስጥ የሚያገኙት የስልጣን ክፍልል የይስሙላ ሆነ ። ይህም ክህደት እንደተፈጸመባቸው እንዲሰማቸው እደረገ። በኋላም ነፍጥ አንስተው ማዕከላዊ መንግስትን እስከ መውጋት ያደረሰ አመጽ ወለደ። ጊዜው የወቅቱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የታላቋን ሶማሊያ ለመምስረት በኬንያ እና ኢትዮጵያ የሚገኙትን የሶማሌ ጎሳዎች የሚኖሩባቸው ምድሮችን መጠቅለልን ዒላማ አድርጎ በእነ አሜሪካ አጋፋሪነት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጀበት ጊዜ ነበር። ወቅቱ የፈጠረው አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ያስገኘላቸው የሶማሊ ላንድ አማጽያን ከብርቱ ትግል እና ፍልሚያ በኋላ ግዛታቸውን በቅኝ ግዛት ዘመን በተሰመረላቸው መስመርነጻነታቸውን አወጁ ። 


ፍጹም መንግስታዊ መዋቅር ፣ ምናልባትም ለአካባቢው ሃገራት ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ በበርካታ ሃገራት ጭምር ተቀባይነት ያገኘችበትም  የራሷ ፓስ ፖርት ያላት ግዛትም ሆነች። ሀገር ብላ ሳትጠራ ሀገር የሆነች ግዛት ሆና ከሶስት ዐሥርተ  ዓመታት ለተሻገረ ጊዜ ቀጠለች ። ይህ በርግጥ ሶማሌ ላንድን አንድ ትልቅ ነገር አሳጥቷታል፥ ሉአላዊ ማንነት ። ይህንን ሉዓላዊ ማንነት ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ለማግኘት ሞክራ የነበረ ቢሆንም  የሶማሊያ መጠነ ሰፊ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ግን ሃሳቡን በጥንስሱ ማስቀረቱ የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው። አሁን እስራኤል በይፋ እውቅናውን ሰጥታታለች። ኢትዮጵያን ከመንገዷ የገታት  የዲፕሎማሲ ዘመቻ እስራኤልንስ ማስቆም ይችል ይሆን? ያጠያይቃል። 
እስራኤል ለሶማሌ ላንዳዉያኑ ዕውቅና ሰጥቻችኋለሁ ማለቷን ተከትሎ ሶማሌ ላንድ በውስጥም በውጭም የሚኖሩ የግዛቲቱ ተወላጆች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል። የግዛቲቱ ፕሬዚደንት አብዲራህማን መሐመድ አቡዱላሂ ኢሮ ለእስራኤል እውቅና በአድናቆኖት የተሞላ ምላሽ ሰጥተዋል። 
«ከ 3 ዐሥርተ ዓመታት በላይ በዘለቀ ሰላም ፣ ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር እና  ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ይዛ ዓለማቀፍ ዕውቅና ስንጠብቅ ከቆየን በኋላ እንደ ሉዓላዊ ነፃ አገር የሰጣችሁንን መደበኛ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተቀብለናል።  ለእስራኤል መንግሥት ያለኝን ልባዊ አድናቆት እገልጻለሁ።»

ከሶማሌ ላንድ ግዛት ፕሬዚዳንት አብዲራህማን መሐመድ አቡዱላሂ
እንደ ሉዓላዊ ነፃ አገር የሰጣችሁንን መደበኛ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተቀብለናል።  ለእስራኤል መንግሥት ያለኝን ልባዊ አድናቆት እገልጻለሁ።»ምስል፦ Monicah Mwangi/REUTERS


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ተጎናጽፈው የሀገርነት ዕውቅና ያገኙ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ሃገራቱ ይህንን መብት ያገኙበት መንገድ እና የሕግ  ትርጓሜው ብቡዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በአንቀጽ 1(2) ሕዝቦች የራሳቸውን የፖለቲካ ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው ሲደነግግ፤  አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ (4) ደግሞ የማንኛውም አገር የግዛት አንድነት ሊከበር እንደሚገባ ያስገድዳል። ይህ ግዛቶች ከሃገራት ተነጥለው ሀገር ለመሆን በሚያደርጉት ትግል ላይ የጎላ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የሶማሊላንድ ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ ዐይታይም። የሶማሌ ላንድን መብት ለማስከበር የሶማሊያን የግዛት አንድነት መናድ ፤ (ሃገራት የተስማሙበትን ቻርተር መናድ) መሆኑ ጉዳዩን ያወሳስበዋል። ወጣም ወረደ ግን ሕግ ሁሌም በሁሉም ላይ እኩል እንደማይሠራ ታሪክ ምስክር ነው።  ዩጎዝላቪያ ወደ ትንንሽ ሃገራት የተበታተነችበት መንገድ፤ ምስራቅ ቲሞር ሃገር የሆነችበት ምሥጢር ቢገለጥ ዕውነታው በታወቀ ነበር። 


የሆነ ሆኖ የእስራኤል በደቡባዊ ቀይ ባህር መገኘት ገና ካሁኑ ውጥረቱን ማጦዙ ግን አልቀረም። ጉዳዩ ከፖለቲካ በላይ ወታደራዊ አንድምታው ትልቅ ነውና ፤ የየመኑ የሁቲ አማጽያን ገና ከአሁኑ በሶማሌ ላንድ  ላይ ዛቻቸውን መሰንዘር ጀምረዋል። እስራኤል ሶማሌ ላንድ ከተገኘች «ዒላማችን ትሆናላችሁ» ሲሉም ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ አሰምተዋል። 
እስራኤል ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ተቃዉሞ እና ዉግዘት ታፈገፍግ ይሆን? ወይስ ልክ እንደ ጋዛው ጦርነት እንደ መካከለኛው ምስራቅ ያሻትን ማድረግ? በዚህኛውም ትገፋበት ይሆን ?  ሶማሌ ላንድስ እስራኤልን ተከትሎ ዕውቅና የሚሰጣት ሌላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገር ታገኝ ይሆን ? እስራኤልን ተከትሎ ዕውቅና ሰጪውስ ሀገር ማን ሊሆን ይችላል? ከድነን እናሳድረው ። 
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ