1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቻይና እና ኢምሬቶች ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ ጉብኝት አንድምታ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ጥር 1 2018

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባለፉት ሁለት ቀናት ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ የተባለን የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለአዲሱ የቻይና-አፍሪካ ማኅበረሰብ ግንባታ የሚውል ነው ተብሎለታል።

https://p.dw.com/p/56bKp
የቻይና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ ትናንት አዲስ አበባን ሲጎበኙ የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት እየተጠናከረ መሆኑን አስታዉቀዋል
ከግራ ወደ ቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና የቻይና መሪ ሺ ጂፒንግ (ቤጂንግ-2017)ምስል፦ Yin Bogu/Xinhua/IMAGO

 

ኢትዮጵያ ለታይዋን የአገርነት ጥያቄ እውቅና በመንፈግ ለቻይና አንድነት ያላትን አጋርነት ገለጸች፡፡ኢትዮጵያ ይህን ያለችው ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር ከተወያዩ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያን የጎበኙት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ሁለቱን አገራት አለማቀፋዊና ቀጣናዊ አበይት ሁነቶች በተፈጠሩቡት ባሁን ወቀት ወደ  ኢትዮጵያ ያመጣቸው ጉዳይ ምን ይሆን?

 

በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባለፉት ሁለት ቀናት ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ የተባለን የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለአዲሱ የቻይና-አፍሪካ ማኅበረሰብ ግንባታ የሚውል ነው ተብሎለታል።

በንግድ፣ በመሠረተ ልማት እና ሌሎችም ዘርፎች ለመተባበር ተስማምተናል ያሉት ሁለቱ አገራት፤ በልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ውስጥ ቅንጅትን የማሳደግ መንገድ ላይ ለመራመድ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋልም ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ “በዓለም ላይ ያለችው አንዲት ቻይና ብቻ ናት በሚል ታይዋን ከቻይና ግዛት የማትነጠል አካሏ ናት” በማለት ለአንድ ቻይና መርሕ ያላትን ፅኑ ድጋፍ በድጋሚ ያረጋገጠችበት ነው ያለው የሁለቱ አገራት የጋራ መግለጫው፤ ቻይናም በፊናዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላላት ሚና ትልቅ ግምት እንደምትሰጥ መግለጽዋ ነው የተሰማው፡፡

አገራቱ በመግለጫቸው፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዛቻ እና ኃይልን መጠቀምን በመቃወም በዚህ ዓመት በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው መካከል አዲስ የፖለቲካ ምክክር ለማድረግም ተስማምተዋል ተብሏልም።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዓለማቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህር ኢንዳለ ንጉሴ፤ የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት የአዲሱ የዓለም ስርዓት ቁልፍ መተወኛ ነው ይላሉ፡፡ “ቻይና ከኢትዮጵያውያን ጋር ስትሰራ ሞዴል አድርጋ የመረጠቻቸው አገራት አሉ፤ ከዚህ አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ለተቀያያሪው ዓለም አዲስ ድፕሎማሲ ማረጋገጫ ለማግኘት ነው በኢትዮጵያ በኩል ወደ አፍሪካ የመጡት” ብለዋል፡፡

የዋንግ ዪ የአፍሪካ ህብረት ውይይት

የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ በአዲስ አበባ ቆይታቸው የቻይና አፍሪካ ትብብርን ለማጠናከር ባለመ ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ጋርም ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅትም የቻይናን የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ከአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ ሁለተኛው የዐሥር ዓመት ትግበራ ጋር በማጣጣም ዘመናዊነትን ለማምጣት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ምክክር መደረጉ ነው የተገለጸው።

የኢትዮ-ቻይና ንግድ ልውውጥ

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድ ልውውጡ ከ13 ቢሊዮን ዶላር መሻገሩን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ስረዳሉ፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንደሚለው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገ በመምጣቱ በሁለቱ ሀገራት ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን ተጠቁሟል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼኽ ሻሽቡዉት ቢን ናሕያንና የኢትዮጵያ አቻቸዉ ጌዲዮን ጢሞ ቲዮስ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሼኽ ሻሽቡዉቲ ቢን ናሕያንና የኢትዮጵያ አቻቸዉ ጌዲዮን ጢሞ ቲዮስምስል፦ The Ethiopian Ministry of Foreign Affairs

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶን የሚያካትት ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአዲሱ የጎርጎሳውያን ዓመት 2026 የመጀመሪያ ጉዟቸውን አፍሪካ ማድረጋቸውም ቻይና በዲፕሎማሲያዋ ለአፍሪካ ትብብር የምትሰጠውን ስፍራ የሚያሳይ ተብሎለታልም፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ኢትዮጵያ እና ቻይና ለአስርት አመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት በቅርቡ ደግሞ በሁኔታዎች ወደ-ማይለዋወጥ የስትራቴጂክ ትብብር ማደጉን በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው አጋርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቻናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦት እና ትራንስፖርት ብሎም አዲስ በመፈጠር ላይ ባሉ ዲጂታል ኢኮኖሚ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ለመተባበር መወያየታቸውንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና አረብ ኢምሬቶች ግንኙነት

በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እየፈጠረች የመጣችው የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፤ የውጭ ጉዳይ መኪኒስትሯን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ “ስልታዊ” የተባለውን የአገራቱን ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አረጋግጠዋል፡፡ ተለዋዋጩ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ሁናቴ በጎላበት ባሁን ወቅት ከኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ምክክር ያደረጉት የኢምሬቶች አቻቸው ሼኸ ሻሕቦት ቢን-ናሃያን በጋራ ሰላም፣ ደህንነት፣ የግዛት አንድነት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ ጠንካራ ያሉት ግንኙነታቸውን አድሰዋል፡፡ በዚህም ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የዓለማቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ባለሙያው እንዳሌ ንጉሴ፤ “ከነዳጅ ጥገኝነት ራሷን በማላቀቅ እየወጡ ካሉ ታላላቅ የዓለም ኢኮኖሚ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም ቢሆን፤ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ኢትዮጵያን በመምረጥ ሁለቱ አገራት በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉና የጉብኝቱም ዓላማ ከዚህ አይርቅም” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና ኢምሬቶች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ መግለጫው በሱዳን ያለው ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዲያመራና በንጹሃን ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ