የፈረንሳይ ግዙፍ የሸቀጥ መደብር ወደ ኢትዮጵያ መግባት ምን ጥቅምና ጉዳት አለው?
ቅዳሜ፣ ጥር 2 2018
ንብረትነቱ የፈረንሳይ የሆነው ግዙፍ የሸቀጥ ግብይት መደብር ካርፉር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ሰሞኑን ተገልጿል።ድርጅቱ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ንብረት ከሆነው ኩዊንስ የሸቀጥ ግብይት መደብር ጋር ባደረገው "የፍራንቻይዝ እና የአቅርቦት ሽርክና" መሰረት ሙያዊ እውቀቶችን እና ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ተስማምቷል።በጉዳዩ ላይ አተያየታቸውን ያጋሩን አንድ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ድርጅቱ "በብዛት ዕቃ አምጥቶ ስለሚሸጥ ተጠቃሚው በተሻለ ዋጋ እንዲሸምት" ያደርጋል ብለዋል። ያም ሆኖ ግን በውል የታሠረ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር የሀገር ውስጥ አስመጭዎችን እና ቸርቻሪዎችን ብሎም አምራቾችን ከገበያ እንዳያስወጡ ያሠጋል ብለዋል።
የዘርፉ ባለሙያ አስተያየት
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የችርቻሮ ግብይት ውስጥ እንዲገቡ ፈቃድ የሰጠው ባለፈው ዓመት ነበር። ይህንን ተከትሎ ካርፉር የተባለው የፈረንሳይ ግዙፍ የሸቀጥ ግብይት መደብር (Supermarket) ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ሰሞነኛ ዜና ነው። የገንዘብ አስተዳደር እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ የውሳኔውን ጥቅም በማብራራት ይጀምራሉ።
"እነሱም በዝቅተኛ ዋጋ - ዲስካውንት ስለሚገዙ ሲሸጡም በተሻለ ዲስካውንት ለተጠቃሚው ያቀርባሉ ተብሎ ይታሰባል። እሱ ነው አንዱ ትልቁ ጥቅም። ሁለተኛ እነዚህ ኩባንያዎች የተበላሹ ዕቃዎች ወይም ለጤና የሚጎዱ ዕቃዎች ያመጣሉ ተብሎ አይታሰብም።"
በሌላ በኩል መንግሥት መሰል ፈቃድ ሲሰጥ የሚገባቸው ውልና ትምምኖች አምራቾችንም የሚጠቅም ሉሆን እንደሚችል ባለሙያው ጠቁመዋል።"የተወሰኑ እቃዎችን ከሀገር ውስጥ ገዝተው እንዲያከፋፍሉ ያደርጋል [መንግሥት]። ምን ማለት ነው የሀገር ውስጥ ዕቃዎችበእነሱ አማካኝነት እንዲሸጡ ለማድረግ ማለት ነው። ያ ምን ያደርጋል ገበያ ስለሚያገኙ ሀገር ውስጥ አምራቾች የተሻለ ምርት ሊያመርቱ ይችላሉ።"
ርምጃው ጉዳት ይኖረው ይሆን?
ባለሙያው እንዳሉት ይህ የውጭ ሀገር የሸቀጦች የግብይት ማዕከል ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባት ጉዳቶችም አሉት።"ጉዳቶች አሉት። እነዚህ ኩባንያዎች በጣም ትልቅ ስለሆኑ የሚያመጡት ዕቃ በጣም በብዛት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ትንንሽ ሱፐር ማርኬቶች ወይም ደግሞ መርካቶ ያሉ ዕቃዎችን የሚሸጡ አስመጪዎች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።"
ሰለሞን ሙጨ
ፀሐይ ጫኔ