1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዝቅተኛ የወለድ ተመን በገበያ እንዲመራ መወሰኑ እና አንደምታ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 30 2018

ብሔራዊ ባንክ የዝቅተኛ ወለድ ተመን ለገበያዉ እንዲተዉና በአስቀማጮች እና በባንኮች ወይም በሌሎች የገንዘብ ተቋማት መካከል በሚደረግ ድርድር እንዲሆን ወስኗል። ይህ ዉሳኔ በገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ምን እንደምታ አለዉ?

https://p.dw.com/p/56WB6
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የብሔራዊ ባንክ በእስላማዊ ባንኮች ላይ ጥሎ የነበረውን የብድር ገደብ የማንሳቱ አንድምታ

ዝቅተኛ የወለድ ተመን በገበያ እንዲመራ መወሰኑ እንደምታው

ብሔራዊ ባንክ የዝቅተኛ ወለድ ተመን ለገበያዉ እንዲተዉና በአስቀማጮች እና በባንኮች ወይም በሌሎች የገንዘብ ተቋማት መካከል በሚደረግ ድርድር እንዲሆን ወስኗል። ይህ ዉሳኔ በገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ምን እንደምታ አለዉ? የኢትዮጵያ ባንኮች ማሕበር ዋና ፀሐፊ አቶ ደምሰው ካሳ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ውሳኔው "በነጋዴዎች ወይም በገንዘብ አስቀማጮች እና በገንዘብ ተቋማት መካከል "መደራደር" እንዲቻል ያደረገ ነው ብለዋል።ይህ ርምጃ "አብዛኛው ነገር በገበያ እንዲወሰን የመደረጉ የመንግሥት ውሳኔ አካል ይመስላል" ያሉ ሌላ የዘርፉ ባለሙያ ደግሞ የገንዘብ የፖሊሲ ለውጡ "የአስቀማጮችን በተወሰነ ደረጃ የተሻለ ወለድ የማግኘት ዕድል ሊጨምር ይችላል" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ውሳኔው "ቁጠባን ሊያበረታታ ይችላል" - ባለሙያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዝቅተኛ የወለድ ተመን በገበያ እንዲመራ ያሳለፈው ዉሳኔ በወለድ በኩል በኢኮኖሚ ዉስጥ የሚዘዋወረዉገንዘብ ላይ ተጽእኖ በማምጣት ያስቀመጠዉ ዋጋን የማረጋጋት አላማ የማሳኪያ መንገድ ተደርጎ ተወስዷል። አቶ አስቻለው ታምሩ 27 ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ የተባለ የግል ተቋም መሥራችና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ናቸው። በባንክ ዘርፍ ውስጥም ለብዙ ዓመታት ሠርተዋል። ይህ ውሳኔ መንግሥት "አብዛኛውን ነገር በገበያ እንዲወሰን የማደረጉ ርምጃ አካል" እንደሆነ ያምናሉ። ይህም ለገንዘብ አስቀማጮች የተሻለ ወለድ የማግኘት ዕድል የሚፈጥርና አማራጭ ይዞ የመጣ ነው።

የኢትዮጵያ ባንኮች ማሕበር በጉዳዩ ላይ ምን ይላል?

ኢትዮጵያባንኮች ማሕበር ዋና ፀሐፊ አቶ ደምሰው ካሳ ለዶቼ ቬለ በሠጡት አስተያየት "በነጋዴ ወይም በገንዘብ አስቀማጮች እና በገንዘብ ተቋማት መካከል ድሮ መደራደር አይቻልም ነበር። አሁን ግን ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በእነዚህ አካላት መካከል የተቀማጭ ገንዘብ ወለድን በተመለከተ መደራደር ይቻላል።" ያም ሆኖ ግን ባንኮች በልዩ ልዩ አማራጮች ለደንበኞቻቸው አሁን በመንግሥት ውሳኔ ከተነሳው ከ7 በመቶ በላይ ወለድ ይከፍሉ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደ እሳቸው ገለፃ ከምንም በላይ አሠራሩ በውጭ ሀገራት የተለመደ ነው። የውጭ ሀገራት ባንኮች በየዕለቱ የወለድ መጠንን በየጋዜጦች እና በየ በራቸው በመለጠፍ ተቀማጭን የሚያበረታታ ብርቱ የውድድር አሠራር  እንደዘረጉ ነግረውናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የባንክ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ ያጋሩት ሐሳብ

በመሰል የገንዘብ እና የምጣኔ ሐብት ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ለሕዝብ በማጋራት የሚታወቁት የባንክ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ ባጋሩት ጽሑፍ የውሳኔውን "ጥቅል ጠንካራ ጎን" ሲገልፁት "የቆጣቢዎችን የመደራደር አቅም ይጨምራል። ለሚያስቀምጡት ገንዘብ  የተሻለ ወለድ እንዲያገኙ ሊያደርግም ይችላል" ብለዋል። አክለውም "ከፍተኛ የሆነ የቁጠባ የወለድ ምጣኔ ፍላጎትን ወጪንና ኢንቨስትመንትን በመቀነስ ቁጠባን ሊያበረታታ ይችላል። የፍላጎት መቀነስ የተመረተና ገበያ የቀረበ ምርት እንዲበዛ በማድረግ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ሰፊ ልዩነት በመፍጠር የዋጋ ንረትን ሊገታ ወይም እንዲቀንስ ሊያግዝ ይችላል።" ሲሉም አብራርተዋል። 

Äthiopien | Geldscheine Währung
ምስል፦ MICHELE SPATARI/AFP

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ውሳኔው "ውድድር ሊቀሰቅስ ይችላል። ዋጋ በመቀነስና በቁጠባ ወለድ ላይ ብቻ የሚመሰረት ነፍስ አድን ግብግብ የተሞላበት ውድድር የቁጠባ ተቀማጭን የወለድ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ሊያንር ይችላል።" በማለት "ጥቅል ደካማ ጎን" ያሉትን አመልክተዋል። እንደ ባለሙያው ትንተና ይህ ፖሊሲ "መበደርን ውድና የማይቻል በማድረግ ተበዳሪ ላይ የወለድና የወጪ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል፣ ተበዳሪውም በወለድ ንረት ምክንያት የአቅርቦት ዋጋ እንዲጨምር ሊያስገድደው ወይም ተበዳሪውን ከገበያ ውድድር ውጭ ሊያደርገው ይችላል።" ሲሉ የሚኖረውን ጉዳት ጠቁመዋል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ