እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው እውቅና ምን ያስከትል ይሆን?
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 18 2018
እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው እውቅና ምን ያስከትል ይሆን?
እስራኤል ለምስራቅ አፍሪካዊቷ ራስ ገዝ ግዛት ሶማሌላንድ የአገርነት እውቅና የሰጠችው የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን ተከትሎ ውዝግብ የማያጣው የአፍሪካ ቀንድ በአዲስ ክስተት ብቅ ብሏል፡፡
የእስራኤልን እውቅና ተከትሎ በመላው ዓለም የተለያዩ ድምጾች እየተሰሙ ሲሆን በሀርጌሳ ደግሞ ደማቅ ሕዝባዊ የደስታ ትዕይንት ታይቷል።
የአፍሪካ ህብረት እና የባህረሰላጤ ሀገራት ትብብርን ጨምሮ በርካታ አገራት የተቃወሙት የእስራኤል ውሳኔ ለቀጣናው እንዴት ያለ አንድምታ ይኖረዋል?
የእስራኤል ውሳኔ
“ክቡር ፕሬዝዳንት ከማንም አስቀድሞ የሶማሌላንድአገርነትን እውቅና መስጠታችንን በፊርማዬ ማረጋገጤን ለእርሶ በመንገሬ ደስታና ክብር ይሰማኛል፡፡ ይህ ውሳኔያችን በኢኮኖሚው፣ ግብርና እና ማህበራዊ እድገት በትብብር እንድንሰራ የላቀ እድል ይፈጥርልናል፡፡ አሁን በዚህ በእስራኤልም ትልቅ የደስታ ስሜት አለ፡፡ በዚሁ አጋጣሚም ይፋዊ ጉብኝት በእስራኤል እንዲያደርጉ እጋብዝዎታለሁ” ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አብድራሃማን መሀመድ አብደላ አበሰሩ፡፡
ይህንኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተንቀሳቃሽ ምስል መግለጫን ተከትሎ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር ከሶማሌላንድ ፕሬዝዳት አብዱራሃማን መሀመድ አብዱላሂ ጋር በቀጣይ የአምባሳደሮች ምደባ እና ኤምባሲ መክፈት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አሳውቀዋል፡፡ በዚሁም ስምምነቱ ለቀጣናው መረጋጋት ያለውን ፋይዳ ጠቅሰዋል፡፡
የሶማሌላንድ ምላሽ
የእስራኤልን ውሳኔ ተከትሎ የሀርጌሳ ጎዳናን በደስታ ያጨናነቁ ሶማሌላንዳውያን፤ የግዛቲቱን ሰንደቃላማ በማውለብለብ ፌሽታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሶማሌላንድ ፕሬዝዳት አብዱራሃማን መሀመድ አብዱላሂ ባስተላለፉት መልእክትም፤ “ዛሬ የዓለም ደስተኛው ሰው እኔ ነኝ፡፡ ታሪካዊውየሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና የገነባነውን ዴሞክራሲያዊ፣ ህገመንግስታዊ እና የመንግስትነት መዋቅራዊ ክንውኖችን መሰረት ያደረገ ነው ብልን እናምናለን፡፡ በዚህ የሶማሌላንድ አስተዳደራዊ ቁርጠኝነት እምነተት ኖሮዋት ታሪካዊውን የአገርነት እውቅና ለሰጠችን እስራኤል ልባዊ አድናቆቴን እገልጻለሁ” ብለዋል፡፡
የሶማሌላንድ ፕሬዝዳት አብዱራሃማን መሀመድ አብዱላሂ በዚህን ወቅት ለጎረቤት አገራት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለኢጋድ እና የአረብ ሊግን ለመሳሰሉት የመንግስታት ትብብር ጥምረቶች የእውቅና እና የአባልነት ጥያቄያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አሳሳቢው የዲፕሎማሲ ሽኩቻ
የአፍሪካ ህብረት ግን የእስራኤልንእውቅና ተቀባይነት ለመንፈግ አፍታም አልፈጀበትም፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ህብረቱ ለሶማሊያ ግዛታዊ አንድነት የማያወላውል አቋም እንዳለው በማመልከት፤ ሶማሌላንድን አሁንም በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አካልነት እንደሚያውቁአት አስረድተዋል፡፡ ከዚህ የህብረቱ መርህ በተቃራኒ ያሉ ሀሳቦች ተቀባይነት እንደማይኖራቸውም ደምድመዋል፡፡
እንደ ግብጽ፣ ተርክዬ እና ሶማሊያ ያሉ አገራትም የእስራኤል ውሳኔውን ተከትሎ ተቃውሞያቸውን ስያሰሙ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀም የጋራ ስምምነት በመፈራረሟ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያ ግን ብያንስ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ዝምታን መርጣለች፡፡
የእስራኤሉ ውሳኔ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው አንድምታ
የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት በመከታተል ትንታኔዎችን በመስጠት የሚታወቁት መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ የእስራኤሉን ውሳኔ ያልተጠበቀ ብለውታል፡፡ “ምናልባት በዚህ ወር አሜሪካ እውቅና ልትሰት ትችላለች ተብሎ ስጠበቅ ነበር እንጂ የእስራኤሉ ውሳኔ ያልተጠበቀ ነው” ያሉት ተንታኙ፤ ግብጽ የአሰብ ወደብንና የጅቡቲን ዶራሌ ወደብን ለማልማትና ለመገንባት በካይሮ ስምምነት ባኖረችበት ባሁን ወቅት፤ የተሰማው የእስራኤል የሶማሌላንድ አገርነት እውቅና፤ በአፍሪካ ቀንድ በአንድ በኩል እስራኤል፣ ህንድ፣ ኢትዮጵያእና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችን በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ሳውዲአረቢያ እና ሶማሊያን የመሳሰሉ አገራትን በማሰለፍ የጂኦፖለቲካውን ትኩሳት የሚያባብስ ብለውታል፡፡
ውሳኔው ከዚህ በፊት ከሶማሌላንድ ጋር ስምምነት በማኖሯ የዲፕሎማሲ እሰጣገባ ውስጥ ገብታ ለነበረችው ኢትዮጵያ ግን የምስራች ነው ያሉን አብዱራሃማን ኢትዮጵያ አሁን ያሰበችውን ለማግኘት በሰፊ የእድል ጎዳና ላይ ቆማለች ነው ያሉት፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ