ትኩረት በአፍሪካ፤ የሶማሊያ ምርጫና የኡጋንዳ ወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 18 2018
«አንድ ሰው አንድ ድምጽ» መርህ የሶማሊያ ምርጫ
ሶማሊያ «አንድ ሰው አንድ ድምጽ» በሚል መርህ ሐሙስ ታሕሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም የምክርቤት አባላት ምርጫ አካሂዳለች። በዋና ከተማዋ በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ሥር የተከናወነው ምርጫ ከከዚህ በፊቱ የጎሳ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የተለየ ሲሆን «አንድ ሰው አንድ ድምጽ» በሚል መርሕ መራጮች የሚፈልጉትን በካርዳቸው በቀጥታ የሚመርጡበት ሥርአት እንደነበር የሐገሪቱ የምርጫ ኮሞሽን አስታውቋል። የዚያድ ባርሬ መንግስት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር በ1969 ከስልጣን ከተወገ ወዲህ የሶማሊያ መፈራረስን ተከትሎ ላለፉት ከ50 ዓመታት በላይ የቀጥታ ድምፅ አሰጣጥ ስርዓት መሻሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሐገር ሶማልያ ደም አፋሳሽ የጎሳ ግጭት፣ የእስላማዊ ፅንፈኞች ተደጋጋሚ ጥቃቶችና የተፈጥሮ አደጋዎችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች። ከ19.6 ሚልዮን በላይ ያላት ሶማሊያ በተለያዩ ጎሳዎች እና ንኡስ ጎሳዎች የተከፋፈለች ናት። ዲር፣ ዲጊል፣ ዳሮድና ሀዊያ የተባሉ ዋና ዋና ጎሳዎች በሐገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው መሆኑን ይነገራል። በነዚህ ጎሳዎች ያለው ፉክክርም ለሐገሪቱ አለመረጋጋት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ከዋናዎቹ ተርታ እንደሚመደብ የአካባቢው ፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የተለያዩ ችግሮች እየተፈራረቁባት ባለችው ሶማሊያ በየጊዜው ክልላዊና ፕረዚደንታዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች። ከዚህ ቀደም የነበረው የምርጫ ሥርዓት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚከናወን እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። የተለያዩ የጎሳ መሪዎች 275 መቀመጫ ላለው ምክርቤት ተወካዮችን በመምረጥ ነበር ምክርቤቱ የሚቋቋመው። እነዚህ የምክርቤት አባላት ደግሞ የሐገሪቱን ፕረዚደንት ለመሆን ከሚወዳደሩት በቀጥታ ድምጽ በመስጠት ይመርጣሉ።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር በግንቦት 2022 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ በዚህ የምርጫ ሥርአት የተከናወነ ነበር። ከየጎሳው የተወከሉ የእንደራሴዎች በቀጥታ በሰጡት ድምጽ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕረዚደንት ሐሰን ሼክ መሐመድ 214 ድምጽ ሲያገኙ ተቀናቃኛቸው መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ በቅጽል ስማቸው ፎርማጆ ደግሞ 110 ድምጽ አግኝተው ተሸንፈዋል።
በአለፈው ሐሙስ የተካሄደው ምርጫ ግን ከዚህ ለየት ያለ ነበር። የምክርቤት አባላቱ በጎሳ የሚወከሉበት ሥርዓትን በማስቀረት መራጩ ሕዝብ በቀጥታ የሚመርጥበት ሥርዓት ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ እንደገና ተግባራዊ ሆኗል።
የምርጫው ተዋንያን ምን አሉ?
በሞቃድሾ ከተማ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘዋወረው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘጋቢ የምርጫ ጣቢያዎች በመራጮች ረዣዥም ሰልፎች ተጨናንቀው መመልከቱን ዘግቧል። ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲያልቅ መንግስት ከ10,000 በላይ የጸጥታ ሰራተኞችን ያሰማራ ሲሆን የሐገሪቱ አውሮፕላን ማረፊያም ለደህንነት ሲበባል በዕለቱ ዝግ ተደርጎ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል።
የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ፋርሐ ሰይድ ዋታናባዳ በተባለ የምርጫ ክልል ለምክርቤት አባልነት ተወዳድራለች። በድምጽ አሰጣጠ ሥነስርዓት ለጋዜጠኞች በሰጠችው አስተያየት
« ለረዥም ጊዜ ስንጠብቀው የነበረውን የአንድ ሰው አንድ ድምጽ የምርጫ ሥርአት ለማካሄድ በመብቃታችን ዛሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። እስከ አሁን ያለምንም ችግር እየተካሄደ ነው።የተሳካና የደስታ ምርጫ እንዲሆን በተስፋ እየጠበቅን ነው።»
በምርጫው ለመሳተፍ ከግማሽ ሚልዮን በላይ መራጮች ካርድ መውሰዳቸውን የሶማሊያ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። የኮሚሽኑ የበላይ ሀላፊ ዓብደልከሪም አሕመድ ሐሰን ምርጫውን እየተዘዋወሩ ይታዘቡ በነበረበት አንድ የምርጫ ጣቢያ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ቀኑን ታሪካዊ ብለውታል።
«ምርጫው ጧት 12 ሰዓት ተጀምሮ ማታ 12 ሰዓት ተጠናቋል። አሁን በምርጫ ጣቢያው የሚገኙ ጥቂት መራጮች በምርጫ ሕጉ መሰረት ይስተናገዳሉ። አሁን ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ እየገባን ነው። የበንዲር ዞን ለምክር ቤት አባላት የተወዳደሩትን የምርጫ ውጤት ቆጠራ። በምርጫ ሕጉ እንደተደነገገው የምርጫ ቆጠራው በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት መጠናቀቅ አለበት። ቆጠራው የሚካሄደውም በምርጫ ጣቢያዎቹ ነው።»
ለምክር ቤት አባላት ዕጩዎች ድምጽ ከሰጡት መካከል አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕረዚደንት ሐሰን ሸኽ መሐመድ ይገኙበታል። እሳቸው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ሶማሊያ ወደ ሙሉ ሰላም የሚወስዳት አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች ሲሉ ተደምጠዋል።
«ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሰላማዊት ሶማሊያ የሚያሸጋግረን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። መሪዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመረጡበት መንገድ ላይ እየተራመድን ነው። እንደ አላህ ፈቃድ ወደተሻለ ደረጃ እንደርሳለን።»
ምርጫው ሶማሊያን ወደ ዴሞክራሲ ያመራት ይሁን?
390 የምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ በአጠቃላይ 1,605 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። ይህ በአዲሱ የመራጮች የቀጥታ ድምጽ አሰጣጥ የተካሄደው የምክርቤት አባላት ምርጫ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በግንቦት 2026 የሚካሄደው ፕረዚደንታዊ ምርጫ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሊያደርገው እንደሚችል ግምታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ቢኖሩም የደህንነት ተንታኟ ሰሚራ ጋኢድ ግን ይህን አብዝተው ይጠራጠራሉ። አሁን የተካሄደው ምርጫ ሶማሊያን ወደ ዴሞክራሲ ያሻግራታል ብለው እንደማያምኑ በማከል።
«በምርጫው የስቪሎች ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው። የምርጫ ሂደቱ የመንግስትና የጸጥታ ሐይሎች ክንውን ነው። የመራጮች ምዝገባም የተሳካ አልነበረም።»
ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በበኩሉ የአሁኑ ምርጫ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2021 የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ እንዳይደገም ስጋቱን ገልጿል። በዚሁ አመት የወቅቱ ፕረዚደንት የነበሩት መሐመድ ዓብዱላሂ ፎርማጆ የስልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት ፓርላመንታዊና ፕረዚደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ አቅደው የነበረ ሲሆን ወደ ከፍተኛ የጎሳ ብጥብጥ አምርቶ እንደነበር ቡድኑ አስታውሷል። በመሆኑም በቀጣዩ የ2026 ፕረዚደንታዊ ምርጫ አካሄድ ከጎሳ መሪዎቹና ከተቃዋሚዎች ጋር ግልጽ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ምርጫው ቢካሄድ ሌላ ቀውስ እንዳይፈጥር ስጋቱን ገልጿል።
በኡጋንዳ የሚገኙ ወጣቶች የፖለቲካ ድርሻ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው
ኡጋንዳ በወጣቶች ብዛት የምትታወቅ አገር ነች ። አብዛኛው ሕዝቧ ከ35 ዓመት በታች ቢሆንም የፖለቲካ ሥልጣን ግን ለአሥርት ዓመታት በገዙት አንጋፋ መሪዎች እጅ ነው።
የዶይቼቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት «77 በመቶ» የተሰኘ ዝግጅት በዩጋንዳ የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ የጎዳና ላይ ክርክር የተሳተፉ ወጣት ፖለቲከኞች ፣ የፖለቲካ አራማጆችና ተንታኞች የኡጋንዳ የፖለቲካ ሥርዓት ትርጉም ያለው የወጣቶችን ተሳትፎን ይፈቅዳል ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተው ተወያይተዋል።
የኡጋንዳ ፓርላማ ከ550 በላይ አባላት ቢኖሩትም ለወጣት ተወካዮች የተያዙት አምስት መቀመጫዎች ብቻ ናቸው። የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት ይህ የወንበር ድልድል የሃገሪቱን የሥነሕዝብ አወቃቀር የማያንጸባርቅ ነው።
የሐገሪቱ ሕገ መንግሥት የወጣቶችን ልዩ ጥቅም እውቅና የሚሰጥ ቢሆንም ተቺዎች ግን እውቅና ማግኘታቸው ተጽዕኖአቸውን ከማጎልበት ይልቅ ይገድባል ብለው ይከራከራሉ ።
አንድ ተሳታፊ « እኛን ወጣቶችን ያገለለ ወታደራዊ አገዛዝ ሥር ነው የምንገኘው» በማለት ሐሳቡን አጋርቷል። ብዙ ተናጋሪዎችም የፖለቲካ ምሕዳሩን «ገዳቢ» ሲሉ ይገልጹታል።
የኡጋንዳ የጥር 2026 ምርጫ የሥርዓት መሰናክል ተጋርጦበታል
ዩጋንዳ በየጊዜው ምርጫ የምታካሂድ ሕገ መንግሥታዊ ሪፐብሊክ ስትሆን ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ ደግሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በጥር 15 ቀን 2026 ለማካሄድ አቅዳለች። እ.ኤ.አ ከ1986 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አሁንም በምርጫው እንደሚሳተፉ አሳውቀዋል።
በሐገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች ከህዝቡ አብዛኛው የሆነውን የወጣቱን ክፍል ያገለለ መሆኑን ብዙዎች ይተቻሉ። መሪዎች ለረዣዥም ዓመታት የስልጣን እርካብ ላይ ተቆናጠው ስልጣን ለተተኪው ትውልድ እንደማያስተላልፉ በማከል።
የሕግ ባለሙያና ከዚህ ቀደም ለፕረዚደንትነት ለመወዳደር አቅዳ ያልተሳካላት ይቮኔ ምፓምባራ ለፕሬዝዳንትነት የመወዳደር ዓላማዋ አለመሳካቱን ሥርዓታዊ መሰናክል መሆኑን ታምናለች።
« አሁን የፖለቲካ ተወዳዳሪ አደለሁም፤ ከዚህ በፊት ግን የፕረዚደንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ነበርኩ። ግን እንድሰረዝ ተደርጓል። በሐገሪቱ ታሪክ የኡጋንዳ ሴት ወጣት ፕረዚደንት የመሆን ተስፋ ነበረኝ። ይሁንና በሥርአቱ ከውድድሩ በመውጣቴ ተወዳዳሪዎች በሙሉ ወንዶች ነበሩ። ምርጫው አሁናዊ የሥነ ሕዝብ መዋቅሩን በተለይ የወጣቱን ውክልና የማያረጋግጥ ነው።»
ምፓምባራ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የደጋፊዎች ፊርማ ማሰባሰብን ጨምሮ የተለያዩ መስፈርቶችን ለማሟላት የምታደርገው ዘመቻ ፈታኝ እንደነበር ገልጻለች።
«ማን ዕጩ ሆኖ እንደሚወዳደር ግልጽ መስፈርት ከማስቀመጥ አንጻር ሥርአቱ ግልጽነት የጎደለው መስሎ ይሰማናል። በተለይም ለውድድር ከሚጠይቋቸው መስፈርቶች አንዱ፤ ከመላው ሐገሪቱ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ይገኝበታል፤ በዚህ ጊዜ በአውሮፕላን ማረፊያዎች የደጋፊዎች ፊርማ ቅጽንና ፋይሎችን መስረቅን ጨምሮ የተለያዩ ሴራዎች አጋጥመውኛል። እነዚ ወደ 5,500 የደጋፊዎቼ ፊርማዎች ያሰባሰብኩባቸው ቅጾች ሁሉ ነው ያጣሁት።»
ምፓምባራ በወቅቱ ለሐገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ስለደረሰባት በደል ሪፖርት ብታደርግም ቅሬታዋ ተቀባይነት እንዳላገኘ ትገልጻለች።
«ምኞት ብቻ በቂ አይደለም»
የወጣቶች መሪ ቸርችል ሳንታሙ በኡጋንዳ ፖለቲካ ለመቀጠል ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለም ይላል። ሳንታሙ «ምኞት አለህ ፣ ቅንዓት አለህ ፣ እውቀት አለህ ፣ ድጋፍ አለህ ፣ ነገር ግን ለመቀጠል የሚያስችል ቴክኒካዊ እርዳታ የለህም» በማለትም አክሏል።
የፖለቲካ ተመራማሪና አስተያየት ሰጪ ዩሱፍ ሴሩንኩማ የኡጋንዳ የአስተዳደር ሥርዓት ከግልጽነት ይልቅ ለፖለቲካዊ ቀጣይነት ቅድሚያ ይሰጣል ሲል ተከራክሯል ።
«የምንኖረው በዘመናዊ አምባገነንነት ነው» ያለው ዩሱፍ «እየተመለከትነው ያለነው የነበረውን ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት እንጂ ለወጣቶች ክፍት የማድረግ አደለም» ብሏል።
ሰርኩማ የተባለው የውይይቱ ተሳታፊ በበኩሉ የምርጫ ሕጎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ፤ የምርጫ ሂደቶችንና የአደረጃጀት መስፈርቶችም በፖለቲካው ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ፖለቲከኞች ተመራጭ ናቸው ። መስፈርቱ የተዘጋጀው ባለፉት አምስት ዓመታት ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ሰዎች ነው» በማለት የፖለቲካ ምሕዳሩ ለአዳዲስ ወጣት ፖለቲከኞች የማይመች መሆኑን ሐሳቡን አካፍሏል።
በምርጫ የወጣቶቹ ተጨማሪ ፈተናዎች
ወጣቶች በፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ከፍተኛ ዕንቅፋት ከሆኑት አንዱ የገንዘብ እጥረት እንደሆነ ይታወቃል። በርካታ ተናጋሪዎች ገንዘብና ዓመፅ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ጠባብ እንዳደረገው ተናግረዋል ። የምርጫ ዘመቻው ብዙ ወጪ የሚጠይቅና አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች እውነተኛ የውሳኔ ሰጪነት ኃይል ሳያገኙ እንዲቀሩ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይገልጻል። በሚካሄዱ ምርጫዎች ወጣቶች የዓመጻ ሰለባ እንደሚሆኑ በማከል።
ሌላው ፈተና የአመራር ጥበብ ጉድለት ከዕድሜ ጋር ተያይዞ መተያቱ እንደሆነ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ይሁንና የአመራር ክህሎት ከዕድሜ ጋር እንደማይዛመድ ወጣቱ ሳንታሙ አበክሮ ገልጿል።
ወጣት ሴቶች ደግሞ ተጨማሪ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል ። ለሴቶች ልዩ ድጋፍ መስጠትን በተመለከተ በምክር ቤት ቢጸድቅም በሐገራዊ የስልጣን እርከኖች የሚታዩ ሴቶች ግን እምብዛም እንደሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ይገልጻሉ።
በኡጋንዳ የፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ አገዛዝ የበላይነት
የውይይቱ ተሳታፊዎች በፕሬዘዳንት ሙሴቪኒ ሥር የነበሩ አሥርት ዓመታት የሕዝብን የሥልጣን ግንዛቤ እንዴት እንደለወጡ አብራርተዋል ። አንድ የውይይቱ ተሳታፊ «ድንገት መንገድ ላይ የምታገኙአቸው ኡጋንዳውያን መሪያችን ማን እንደሆነ ብትጠይቋቸው ብዙዎቹ ሙሴቬኒን እንደሚሏችሁ እርግጠኛ ነኝ» ሲል በሕዝቡ ዘንድ ስልጣን ለፕረዚደንት ሙሰቬኒ ብቻ የተሰጠ የሚያስመስል እሳቤ መስረጹን ተናግሯል።
መፍትሔውስ?
ዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ባዘጋጀው የፖለቲካ አራማጆችና ፖለቲከኞች የጎዳና ላይ ውይይት ተሳታፊዎች ለኡጋንዳ የፖለቲካ ምሕዳር መጥበብና የወጣቶች የስልጣን ተሳትፎ ማነስ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ሀሳቦችንም ሰንዝረዋል። አንዳንዶቹ የለውጥ ስራዎች፣ የገንዘብ ድጋፍ ፣ ጠንካራ ተቋም ግንባታና የዜግነት ትምህርት ዘመቻ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል ። ሌሎች ደግሞ የፖለቲካ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው ሐሳባቸውን አንጸባርቀዋል።
«ችግሮቻችን ቴክኒካዊ አይደሉም» ያለው ወጣት ሰርኩማ «የኛ ችግሮች ፖለቲካዊ ናቸው» ብሏል። ስለሆነም ከቴክኒካዊ ጉዳዮች ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ነው ሐሳቡን ያንጸባረቀው። ሌላው ወጣት የፖለቲካ አራማጅ ቸርችል በበኩሉ የፖለቲካ ምሕዳሩ ሥርዓታዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
« እኔ እንደማምነው የፖለቲካ ምህዳሩ ሥርአታዊ ቅርጽ መያዝ አለበት። ሥርዓታዊ መዋቅር መዘርጋት ትልቁ ነጥብ ይመስለኛል»
አንድ ተሳታፊ በበኩሉ ሐገሪቱን ለምን በዕድሜ የጠገቡት ብቻ ይመራሉ? የሚል ጥያቄም ጭሯል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ