1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኮሬ ዞን የምርጫ ጣቢያዎች መሠረዛቸዉን ኢዜማ ተቃወመ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ጥር 1 2018

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት ሦስቱ የምርጫ ጣቢዎች በክልሉ ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጀሎ እና ዶርባዴ ተብለው በሚጠሩ ቀበሌያት ውስጥ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡

https://p.dw.com/p/56ahs
የኮሬ ዞን ሦስት የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ከሚካሄድባቸው ዝርዝር መሠረዘቸዉን ኢዜማ ተቃወመ
(ከክምችታችን) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ መሪ ብርሐኑ ነጋ ሥለ ፓርቲያቸዉ ምብራሪያ ሲሰጡ።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

በኮሬ ዞን የምርጫ ጣቢያዎች መሠረዛቸዉን ኢዜማ ተቃወመ

 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ  “ ሠፊ ማህበራዊ መሠረት አለኝ “ ባላቸው የኮሬ ዞን ሦስት የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ከሚካሄድባቸው ዝርዝር ውጭ መደረጋቸው አግባብ አይደለም ሲል ተቃወመ ፡፡ የምርጫ ጣቢያዎቹ ቀደምሲል 6ኛው አገራዊ ምርጫ የተካሄደባቸው መሆናቸውን የጠቀሰው ፓርቲው ነገር ግን በዘንድሮው 7ኛው አገራዊ ምርጫ እንዳልተካተቱ ገልጿል ፡፡ይህም  የህዝቡን የመምረጥ መብት የሚነፍግ በመሆኑ ቦርዱ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው ፓርቲው ጠይቋል  ፡፡

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ የቀሩት  ሦስቱ የምርጫ ጣቢዎች በክልሉ ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጀሎ እና ዶርባዴ ተብለው በሚጠሩ ቀበሌያት ውስጥ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡  ቀበሌያቱ ከአሁን በፊት ምርጫ ሲካሄድባቸው የቆዩ መሆናቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት  በፓርቲው የኮሬ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ ቃኤል ቡሱአ የቦርዱ ውሳኔ ጥያቄ ፈጥሮብናል ይላሉ ፡፡

የፓርቲው ሥጋቶች

የምርጫ ጣቢያዎቹ በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው 7ኛው አገራዊ ምርጫ ዝርዝር ውስጥ አለመግባት ሁለት አይነት ተፅእኖዎች ሊያሳድር እንደሚችል በፓርቲው የኮሬ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ ቃኤል ቡሱአ ሥጋታቸውን ገልጸዋል ፡፡ የመጀመሪያው ህዝቡ ተወካዮቹን ለመምረጥ ህገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን መብት እንዳይጠቀም ያደረገዋል ያሉት ሊቀመንበሩ “ በሁለተኛ ደረጃ  ቀበሌያቱ ሠፊ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎቻችን ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው  ፡፡ ይህ ማለት በቀጣይ በምርጫው በምናደርገው ፉክክር ላይ የፍትሃዊነት መጓደል ያስከትልብናል ብለን እናምናለን “ ብለዋል ፡፡

ዶክተር አወቀ ሃምዛዬ በ2013 ዓም በተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የኢዜማ ፓርቲን ወክለው በእጩነት የቀረቡት በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ነበር ፡፡ በወረዳው አብላጫ ድምፅ በማግኘት አሁን ላይ  በተወካዮች ምክር ቤት ገብተው በአባልነት እያገለገሉ ይገኛሉ ፡፡ ቦርዱ ጣቢያዎቹን በምን መመዘኛ እንደተዋቸው ፓርቲው በደብዳቤ መጠየቁን  የጠቀሱት ዶክተር አወቀ “ ቦርዱ ጥያቄያችንን በመቀበል ውሳኔው እንደገና ያየዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን “ ብለዋል ፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሬ ዞን የነበሩ 3 የምርጫ ጣቢያዎችን ለዘንድሮዉ ምርጫ አለማካተቱትን ኢዜማ ተቃወመ
አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና መሥሪያ ቤትምስል፦ Solomon Muchie/DW

የአስቻይ ሁኔታዎች ልየታ

ዶቼ ቬለ በፓርቲው ቅሬታ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አስተያየት ለማካተት  በሥልክም ሆነ አጭር የጹሁፍ መልዕክት በመላክ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ያም ሆኖ ቦርዱ ምርጫውን ለመካሄድ  አስቻይ ሁኔታ ያለባቸውን አካባቢዎች ለመለየት ከክልል መንግሥታት እና ከከተማ መስተዳድሮች የፀጥታ ተቋማት ጋር መረጃዎችን እንደሚያሰባስብ ቀደምሲል ገልጾ ነበር ፡፡ በቦርዱ መግለጫ መሠረት አረንጓዴ ቀለም ምርጫ ማድረግ ይቻላል ፣ ቢጫ ከጥንቃቄ ጋር ምርጫ ማድረግ ይቻላል ፣ ቀይ ደግሞ ምርጫ ማድረግ አይቻልም በሚል ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን እንደሚበይን መግለጹ ይታወሳል ፡፡

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ