1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኮሬ ዞን ተፈናቃዮች አቤቱታ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2018

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ቀደመ ቦታቸው ባለመመለሳቸው ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገናል አሉ ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ለመመለስ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት መንግሥትን ቢጠይቁም እስከአሁን ተግባራዊ ሊያደርግ አልቻለም ፡፡

https://p.dw.com/p/56LhX
ኮሬ ከተማ
ኮሬ ከተማ ምስል፦ Shewangizaw Wogayehu/DW

የኮሬ ዞን ተፈናቃዮች አቤቱታ

የኮሬ ዞን ተፈናቃዮች አቤቱታ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ቀደመ ቦታቸው ባለመመለሳቸው ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርገናል አሉ ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ለመመለስ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት መንግሥትን ቢጠይቁም እስከአሁን ተግባራዊ ሊያደርግ አልቻለም።

ቁጥራቸው 12 ሺህ 182 የሆኑት እነዚሁ ነዋሪዎች በ2009 ዓ.ም የተፈናቀሉት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጀሎ እና ዶርባዴ ከተባሉ ቀበሌያት ነው ፡፡ በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሚያደርስባቸው ጥቃት መንደራቸውን ለመልቀቅ ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ተፈናቃዮቹ “  ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ እየኖርን እንገኛለን  ፡፡ ወደ ቦታችን ለመመለስ ለመንግሥት ያቀረብነው ጥያቄም እስከአሁን ምላሽ አላገኘም “ ብለዋል  ፡፡

የአካባቢው አስተዳደር ተፈናቃቹን መመለስ ለምን ተሳነው ?

የተፈናቀሉት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢያዎቹ ለመመለስ ያልቻሉት ሁለቱ  የደቡብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ተጎራባች  ክልሎች  ሁኔታውን ለማስተካከል ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው ሲሉ ወቅሰዋል ፡፡ በአካባቢው “ ሸኔ” እየተባሉ የሚጠሩ ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ የተናገሩት ተፈናቃዮቹ “ መንግሥት በእነዚህን ሁለት ቀበሌያት ተንቀሳቅሶ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ያቅተዋል ብለን አናምንም ፡፡ ነገር ግን ትልቁ  ችግር የደቡብ ኢትዮጵያ እናየኦሮሚያ ተጎራባች ክልሎች ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው ነው “ ብለዋል ፡፡

የኮሬ ዞን አስተዳደር ምላሽ

ዶቼ ቬለ የተፈናቃዮቹን ቅሬታ አስመልክቶ ያነጋገራቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ የሁለቱ ክልል መስተዳድሮች ለተፈናቃዮቹ ትኩረት አልሰጡም የሚለውን ወቀሳ አይቀበሉትም ፡፡ ይልቁንም ተፈናቃዮቹን በተያዘው ዓመት ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ  ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል ፡፡

ፎቶ ከማህደር፤ ኮሬ ዞን
ፎቶ ከማህደር፤ ኮሬ ዞን ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ተፈናቃዮቹን ለመመለስ የፀጥታው ሁኔታ ይፈቅዳል ወይ ? የወደሙ መሠረተ ልማቶችስ መልሰው ተገንብተዋል ወይ ?  በሚል ከዶቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ  ዋና አስተዳዳሪው “ ፀጥታን በተመለከተ በኮሬ እና ከምዕራብ ጉጂ ዞን መስተዳድሮች በኩል የጋራ መግባባት ተደርሶ ጥምር የሰላም ግብረሃይል ተቋቁ‑ እየተሠራ ይገኛል ፡፡ የጠፉ የመሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመተካት የግንባታ ቁሳቁሶች እየተሰበሰቡ እንደሚገኙና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር በኩል ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ተግብቷል “ በማለት ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ