1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

"ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በምስረታ ላይ መሆኑ ተገለፀ

ቅዳሜ፣ ጥር 2 2018

ጊዜያዊ መጠሪያውን"ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" ብሎ የሰየመ አዲስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ በምሥረታ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሰብሳቢነት የመሩት እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ደስታ ዲንቃ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/56cfq

አቶ ደስታ ዲንቃ፤ የቀድሞ የኦፌኮ አባል
አቶ ደስታ ዲንቃ፤ የቀድሞ የኦፌኮ አባል እና የአዲሱ ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መስራችምስል፦ Desta Dinka via Seyoum Getu DW

"ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በምስረታ ላይ መሆኑ ተገለፀ

ጊዜያዊ ስያሜውን "ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" ብሎ የሰየመ አዲስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት በምሥረታ ላይ መሆኑን የሀሳቡ ጠንሳሽ እና ሂደቱን የሚያስተባብሩት ግለሰብ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሰብሳቢነት የመሩት እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ደስታ ዲንቃ "ፖለቲካችን በማስተዋል የተሞላ እና ሕዝብን እና ሀገርን ማዕከል ባደረገ አኳዃን እየተያዘ ባለመሆኑ" ይህንን ለመለወጥ ድርጅት ወደ መመሥረት መግባታቸውን ተናግረዋል።የፓርቲ ምሥረታ ሥራው ከአንድ ዓመት በፊት መጀመሩን የገለፁት አስተባባሪው የ10 ሺህ አባላት ስብሰባ ተጠናቋል፣ መተዳደርያ ደንብ፣ አርማ፣ ስያሜ እና የመመስረቻ ጽሑፍም ተዘጋጅቷል" ብለዋል።// 

የሕዝብ እና የሀገር ጥያቄ ሳይስተካከል እየቀረ መሆኑ ወደ ፓርቲ ምስረታ ገፍቶናል

ፖለቲከኛ ደስታ ዲንቃ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት "ፌደራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ" በሁለት የኦፌኮ የቀድሞ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በሥራ አሥፈጻሚ ውስጥ የነበሩ ሰዎች እና ሌሎችም ነው እየተቋቋመ ያለው።

በመንግሥት በኩል "ካለፈው አለመማር እና ተመሳሳይ የፖለቲካ አስተዳደርን መያዝ"፣ በተቃውሞው ጎራም ቢሆን "ይዘው የወጡትን የትግል መስመር እየለቀቁ አዲስ ወደሚመጣው ሥርዓት እየገቡ ለራሳቸው ረፍት የሚሰጡበት" ነባራዊ ኹኔታ መኖሩ፣ አልፎም "የሕዝብ እና የሀገር ጥያቄ ሳይስተካከል እየቀረ ዛሬ ላይ በመድረሳችን" ይህንን ፓርቲ እያቋቋምን ነው ብለዋል።

ፖለቲከኛው እንዳሉት በዚህ ምክንያት "የሕግ የበላይነት እና ሕግን ማክበር" እየጠፋ ግንኙነቶች "ከሕግ ውጪ በሆነ አኳዃን ስለሚደረጉ ኃላፊነትና ተጠያቂነትም የለም።" እናም ውጥኑ ተሳክቶ ፓርቲው  የሚመሠረት ከሆነ ሕግና ሕግን መሠረት ያደረጋ ሥራ እንሠራለን ብለዋል።

በቀጣዩ ምርጫ ስለመሳተፋችን "እርግጠኛ አይደለሁም"


የፓርቲ ምስረታ የመጀመርያ እንቅስቃሴያቸው በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ መሳተፍን አልሞ እንደነበር የነገሩን አቶ ደስታ አሁን ባለንበት ኹኔታ ግን በቀጣዩ ምርጫ ስለመሳተፋችን "እርግጠኛ አይደለሁም" ብለዋል። በዚህ ዓመት የሚደረገው ምርጫ ካለፈው በባሰ "የተጣበበ ኹኔታ" የሚደረግ እና "አጓጊ ያልሆነ" በመሆኑ ባንሳተፍም የሚያስቆጭ አይደለም ሲሉም የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት ዝግጅት ስለ ማጠናቀቃቸው ጠቅሰዋል።

አዲስ ፓርቲ መመስረት ለምን አፈለገ?

አቶ ደስታን አዲስ ፓርቲ መመስረት ለሕዝብ ከጥቅሙ ጉዳቱ አያመዝንም ወይ ብለን ጠይቀናቸው ነበር። የፖለቲካ ምኅዳሩ አለመስተካከልና ሕዝብ ነፃ ሆኖ ያለምን ፍርሃት የፖለቲካ ተሳትፎ እያደረገ አለመሆን፣ የዜጎች የአመለካከት ነፃነት አለመኖር፣ "ብዙ የሚባሉት የፖለቲካ ድርጅትቶች" የሕዝብ ድምፅ መሆን አለመቻላቸል፣ በመካከላቸውም የመገፈታተር እንጂ የመተጋገዝ ምልድ አለመዳበሩ፣ የዜጎችን እና የሀገርን ችግር ለመፍታት በቁጠኝነት አለመታገላቸው፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በብሔር ሥም እየተደራጁ መስራቾችን የሚጠቅም ሥራ ላይ መሠማራታቸው በሀገሪቱ ነባራዊ ኹኔታ አዲስ ፓርቲ መመሥረትን ተወቃሽ አያደርገውም ብለዋል።

ሰለሞን ሙጨ

ፀሐይ ጫኔ