የ”ማይ ጉሊት” ተፈናቃዮች አቤቱታ
ቅዳሜ፣ መስከረም 24 2018
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ “ማይ ጉሊት” በተባለ አካባቢ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን አመለከቱ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የምግብ አቅርቦት ችግር ባይኖርም የመድኃኒትና ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል እንደሚሰራ ገልጧል፡፡
ከ4 ዓመታት በፊት ማንነት ተኮር በሆነ ግጭት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ አቅራቢያ “ማይ ጉሊት” በተባለ አካባቢ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ለምግብ፣ ለመድኃኒትና ለመጠለያ እጦት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ባልተጠናቀቀ የግንባታ ቦታ ውስጥ በብርድ፣ በነፋስና ብዝናብተጋልጠው በጋራ እንደሚኖሩ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ ይህም ለተለያዩ ችግሮች እንደዳረጋቸው አመልክተዋል፡፡ ከተፈናቃዮች መካከል አንዱ ተፈናቃዩ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠናል” ተፈናቃዮች
የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር እንደሌለ ያስረዱን እኚህ ተፈናቃይ፣ ችግሮች የበዙ ናቸው ብለዋል፣ ከ4 ዓመት በፊት ይኖሩበት ከነበረው የምስራቅ ወለጋ ዞን “ጉዱ ሶዮ” ወረዳ፣ “ዓለም ሰዬ” ቀበሌ እንደሆነ አስታውሰው፣ ሲወጡ የለበሱትን ልብስ ለብሰው እንደወጡና ያን መቀየር ባለመቻላቸው ከነቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ የምግብ እጦቱም ከፍተኛ በመሆኑ “ድረሱልን” የሚል ድምፅ አሰምተዋል፡፡ ማይ ጉሊት በተባለው አካባቢ ከ5ሺህ 300 በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ተፈናቃዩ ተናግረዋል፡፡
ሌለዋ ተፈናቃይ በበኩላቸው ከ40 ዓመት በላይ ከኖሩበት የወለጋ አካባቢ ምንም ነገር ይዘው እንዳልወጡ አመልክተው የአልባሳትም ሆነ የምግብ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጪ በቂ የሚባል እርዳታ ከመንግሥት እንደማይቀርብላቸውም አክለዋል፡፡ በአካባቢው የቀን ሥራ ለመስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ከወጣት እስከ ሽማግሌ ያለሥራ ቁጭ ብሎ ይውላል ያሉን ሌላ ተፈናቃይ፣ ስድስትና ሰባት ቤተስብ ያላቸው ሠዎች ኑሯችውን ሊመሩ አልቻሉትም፣ የእርዳታ እህል ከወሰዱም ወራት ማለፉን ነው የሚናገሩት፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው፣ እርዳታ የወሰዱት ባለፈው ግንቦት ወይም ሰኔ ነው፡፡
በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በበኩላቸው ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው የመጡ 2,000 ያክል ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው ይኖሩበት የነበረው አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ ተሻሸሎ ወደነበሩበት እስኪመለሱ ድረስ እርዳታ አይቋረጥባቸውም ብለዋል፡፡
“የምግብ አቅረቦት ችግር የለም” የዋግኽምራ አደጋ መከላክል
“የምግብ እርዳታ አቅርቦት ችግር የለም” ያሉት አቶ ምህረት የመድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ ከአጋር አካላት ጋር እየተነጋገሩበት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ መኖሪያን በተመለከተ በእርግጥ ችግር ቢኖርም ተፈናቃዮቹ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መኖር እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት።ተፈናቃይ በመጠለያ ማኖርም እየቀረ እንደሆነ ገልፀዋል፣ ምክንያት ያሉት ደግሞ ተፈናቃይ ያልሆኑ ሠዎች ወደ ተፈናቃይ መጠለያ በመግባት ያልተገባ ያሉትን ጥቅም እየፈለጉ በመሆኑ ያን ለመከላከል እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
በአማራ ክልል ከተላያዩ ክልሎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ቀያቸውን ለቅቀው የመጡ ከ640ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር