ቀውስ በጊኒ ቢሳዉ፦ ኤኮዋስ ምን መፍጠር ይችል ይሆን?
ሐሙስ፣ ኅዳር 25 2018
ጊኒ ቢሳዉ ውስጥ ባለፈው ረቡዕ (ኅዳር 17 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) የተፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ያስከተለው ቀውስ እንደቀጠለ ነው ። በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱ ቁጣቸውን የሚገልጡ ተቃዋሚዎች አሁንም ድምፃቸውን እያሰሙ ነው ።
«አምባገነንነት ይውደም! ነጻነት ለዘለዓለም ይኑር! ነፃነት ለዘለዓለም ይኑር!»
ቀውሱን ለመፍታት በሚል የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማኅበረሰብ (ECOWAS) ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ሰኞ ዕለት (ኅዳር 22 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) ወደ ቢሳው ተጉዞ ነበር ። ከፍተኛ ልዑካኑን የመሩት በአሁኑ ወቅት የኤኮዋስ ሊቀመንበርነቱ ተራ የደረሳት ሴራሊዮን ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ ናቸው ።
ወደ ጊኒ ቢሳዉ ያቀናው የልዑካን ቡድን ውስጥ የኤኮዋስ ኮሚሽን ፕሬዚደንት የጋምቢያ የቀድውሞ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ዖማር ዓሊዩ፣ በቢሳዉ የኢኮዋስ ተወካይ ንጎይ ኡካኤጄ እንዲሁም በምዕራብ አፍሪቃ የተመድ ተወካይ ሌዎናርዶ ሲማዎ ይገኙበታል ። ልዑኩን የመሩት ጁሊየስ ማዳ ባዮ ቢሳዉ ውስጥ ወታደራዊ አመራሩን ከማነጋገራቸው በፊት እንደገለጡት ከሆነ፦ «ቀውሱን በቅርብ ለመከታተል ብቻ ሳይሆን በንቃት ለመርዳት» ወስነዋል ። የጊኒ ቢሳዎ የተቃውሞ ሰልፈኞች ግን በቢሳዉ ጎዳናዎች ቁጣቸውን እየገለጡ ነው ። «ፖ ዲ ቴራ» በመባል የሚታወቀው ንቅናቄ መሪ ቪጋሪዮ ሉዊሽ ባላንታ ተቃውሞውን እንደማያቋርጡ አሳስበዋል ።
«በተቃውሞው እንገፋበታለን፣ ሕዝባዊ ንቅናቄውን እንቀጥላለን፣ ለሕዝቡም እንታገላለን። ለመከላከያ ኃይላት ከፍተኛ አዛዥ እና ጊዜያዊ መንግስት የሕዝብ ሕጋዊ ይሁንታ ስለሌላቸው አሁንም ወደመጡበት የመመለስ እድል እንዳላቸው እንገልፃለን ።»
ኤኮዋስ እሁድ ኅዳር 14 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ውጤት ይፋ እንዲሆን አሳስቧል ። በጊኒ ቢሳውም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በፍጥነት ወደነበረበት እንዲመለስ እየጠየቀ ነው ።
ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆርታ ኢንታ-ኤ ግልጽ ግቦችን አስቀምጠዋል
ጊኒ ቢሳው ውስጥ የሽግግር መንግስቱ በጄኔራል ሆርታ ንታምን ስር ተቋቁሞ ግልፅ ዓላማዎቼ ያላቸውን ነጥቦች ይፋ አድርጓል ። ሙስናን እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን በመዋጋት ረገድ አንዳችም ትእግስት እንደማይኖር ጄኔራሉ ሥልጣኑን በተረከቡበት ወቅት አሳስበዋል።
«ሦስት ነገሮችን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፥ በመጀመሪያ፦ የሕዝብ ንብረቶች አያያዝ ላይ ጥብቅ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ ሁለተኛ፦ ሙስናን እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን በመዋጋት ረገድ አንዳችም ትእግስት እንዳይኖር፣ ሦስተኛ፦ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የመመለስ ሂደቱ መጠናቀቅ አለበት ። ያም ዋናው ተግባራችን መሆን አለበት ።»
ከሥልጣናቸው ተነስተው ወደ ሴኔጋል የሸሹት የጊኒ ቢሳዉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ዓርብ ዕለት ወደ ኮንጎ ብራዛቪል ተጉዘዋል ። ጉዟቸውም በኮንጎው ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጌሶ ግብዣ መሆኑ ይፋ ሁኗል ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከነቤተሰባቸው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ኅዳር 19 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ኮንጎ ዋና ከተማ የገቡት በኮንጎ መንግስት በተከራየ አውሮፕላን መሆኑም ተገልጧል ።
ወታደራዊው መንግስት አገሪቱን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ እየሞከረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ተቃውሞው እየበረታ ነው ። የፖለቲካ ታዛቢዎች የኤኮዋስ ተልእኮ ፖለቲካዊ መፍትኄ ሊያመጣ አለያም በቢሳው ውስጥ ያሉትን አዲሶቹን ወታደራዊ መሪዎች አካሄዳቸውን እንዲቀይሩ ማሳመን እንደማይችል አድርገው ይመለከታሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ አንቶኒዮ ካሽካሽ
ፀሐይ ጫኔ